AMN – የካቲት 7/2017 ዓ.ም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)ን ዛሬ ማለዳ በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በውይይቱ ዶክተር ጌዲዮን ኢትዮጵያ ለኢጋድ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ እና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ለቀጣናው ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላትን ወሳኝ ሚናም ጠቅሰዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኢጋድ ስትራቴጂካዊ ግቦች ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ወሳኝ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በመግለፅ ኢትዮጵያ ከኢጋድ ጋር ይበልጥ ተቀራርባ እንደምትሠራ አክለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አያይዘውም ኢጋድ በቀጣናው የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት ኢትዮጵያ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።
ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ አዲሱን የኢጋድ ስምምነት በማጽደቋ አመስግነዋል።
ሀገሪቱ እንደ አባል ሀገር ከኢጋድ ጋር ያላትን ወሳኝ ድጋፍ እና ተሳትፎ አጠናክራ እንድትቀጥል መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።