AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
የዓድዋ ድል በኅብረብሔራዊ አንድነት የተገኘ ታላቅ ፍሬ፣ በኢትዮጵያዊነት ወኔ የተቀዳጁት ክቡር አክሊልና ለብሔራዊ ትርክት መሠረት የጣለ የአብሮነት መንፈስ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
አፈጉባዔው ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
የዓድዋ ድል ለአንድ ዓላማ በጽናትና በአብሮነት የመቆም ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በአገራዊ አንድነት የማይደራደሩ፣ ለአመኑበት ነገር ግንባራቸውን የማያጥፉና ፊታቸውን የማይመልሱ መሆናቸውን በገሀድ ያሳየ የአንድነታችን በዓል ነው፡፡
የዓድዋ ድል መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መደማመጥንና ብሔራዊ ስሜትን የሚያስተምር ታላቅ ተቋም ነው።
ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በአመለካከት ሊለያዩ ይችላሉ፤ ሆኖም በአንድ እንዲተሙ የሚያደርግ ብሔራዊ የአብሮነት እሴት አላቸው። ይህ ብሔራዊ የአብሮነት እሴት ትናንት በአባቶቻችን ዘመን በዓድዋ ተራሮች አናት ላይ ግዝፎና ነፍስ ዘርቶ እንደ አጥቢያ ኮከብ የደመቀ የድል ሰንደቅ ሰቅሏል፤ በቅኝ ግዛት ለሚማቅቁት ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችም “እምቢ ለነጻነት” የሚል ወኔ ሰንቋል፤ ዛሬ በእኛ ዘመን ደግሞ በጉባ ሰንሰላታማ ተራሮች ግርጌ ለብዙዎች መብራትና ራት የሚሆን ግዙፍ የታሪክ አሻራ የሚሆን ግድብ ገንብቷል፤ ለተፋሰሱ አገራትም የ“ይቻላል” መንፈስ ፈጥሯል፡፡
በመሆኑም በዘመናት መካከል ፈተናዎችን በድል የተሻገረውንና ለቀሪው ዓለም ትምህርት እየሰጠ የመጣውን መልካም የአብሮነት እሴታችንን ልንከባከበውና ልንጠብቀው፤ ልንኮራበትና ልንኖረው፣ ለቀጣዩ ትውልድም ሳንሸራርፍ ከነክብሩ፣ ሳናጎድል ከነሁለመናው ልናሸጋግረው ይገባል፡፡
የዓድዋ ድል በዘመኑ የተዛባውን የዓለም ፖለቲካ ሚዛን ለማስተካከል ለሚደረገው ትግል የጥሪ ደወል ሆኖ ፈጥኖና ቀድሞ አነቃቅቷል፤ ነጮች በጥቁሮች ላይ የገነቡትን የኃያልነትና የበላይነት ትርክት ከመሠረቱ ንዷል፡፡ በአንጻሩ በድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ የጥቁር ሕዝቦችን ዓይነ ሞራ ገልጧል፤ የጎበጠውንም ወገባቸውን አቃንቷል፡፡ ወደ ነጻነት የሚመራ የብርሐን ቀንዲል ሆኖ አብርቷል፡፡ ወኔ ሆኖ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
የዘንድሮውን በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ሐሳብ ስናከብርም ከፊት ለፊታችን የታጠሩብንን እንቅፋት የሆኑብንን ከፋፋይ ነጠላ ትርክቶች በምክክር በማፍረስ፣ ኅብረብሔራዊ አንድነትችንን በመግባባት ላይ ለመገንባት ልክ እንደ ዓድዋው ድል በውይይት ችግሮቻችን ለመፍታት በይቅርታ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት መቻላችንን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡
የዓድዋ ድል የጥንት ሥልጣኔና የገናና ስም ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያ ከዘመናዊ ዓለም ጋር መልሶ ያገናኘ ድልድይ ነው። ወድቆና ደቆ መቅረት እንጂ ወድቆ መነሳትና ፈርሶ መሠራት መጥፎ ልንለው የሚገባ አይደለም፡፡ በዛሬ አቅም እንጂ በትናንት ስም አይኖርም፡፡ የጥንቱን ሥልጣኔያችንንና የትናንቱን ዓድዋችንን በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ሕያው ሆነው እንዲቀጥሉ ዛሬያችንን በሁሉም መስክ ማሳመር ይኖርብናል፡፡ የዛሬ አቅም ለነገ ስም፣ የዛሬ ጥረት ለነገ ጥሪት ነውና!
በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።