የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮችን ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ የአሰራር ማዕቀፎችን በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ይገባል-ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)

You are currently viewing የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮችን ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ የአሰራር ማዕቀፎችን በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ይገባል-ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)

AMN-ሚያዝያ 18/2017 ዓ.ም

የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮችን ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ የአሰራር ማዕቀፎችን በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ቀልጣፋ ሂደትን መከተል እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

በዋሽንግተን ዲሲ አየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዓለም አቀፉ የሀገራት የዕዳ ውይይት ላይ ተሳትፋለች።

ስብሰባው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋ እንዲሁም በወቅቱ የቡድን 20 ሊቀመንበር በሆነችው ደቡብ አፍሪካ በጋራ የተመራ ነው።

ስብሰባው በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ሂደት የሚገኝበትን ደረጃ በመገምገም የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች አመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በመድረኩ እንደተናገሩት የዕዳ ማዕቀፉ ረጅም ጊዜ ቢወስድም ያለው ፋይዳ ወሳኝ ነው።

ይህም በዛምቢያ፣ ጋና እና አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ የተደረጉት የተሳኩ የዕዳ ሽግሽግ ጥረቶች ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለው በተበዳሪው ሀገር እና በአበዳሪዎች ኮሚቴ መካከል ባለው የመርህ ስምምነት መሰረት የብድር አያያዝ ውሎችና ሁኔታዎችን ይፋ በማድረግ ግልፅ አሰራርን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ አንስተዋል።

በተጨማሪም ከመርህ ስምምነት ጀምሮ ከአበዳሪ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነትና የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም ፈጣንና ቀልጣፋ ሂደት በማመቻቸት አላስፈላጊ መዘግየቶችን መቀነስ ተገቢ መሆኑን በአጽንኦት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በማርች 2025 ከአበዳሪዎች ጋር በመርህ ደረጃ መስማማቷ የሚታወስ ሲሆን እ.አ.አ. በጁን 2025 የመግባቢያ ሰነዱ ዝግጅት እንደሚጠናቀቅ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review