የዜጎችን ህይወት የታደገው የጤና መድህን

You are currently viewing የዜጎችን ህይወት የታደገው የጤና መድህን

የህክምና ገንዘብ በማጣታቸው ከህመማቸው ጋር ረጅም ጊዜ እንደቆዩ ይገልጻሉ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ዘነበ ወርቅ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አምሳል ሀይሉ፡፡ አብሯቸው የቆየውን የረጅም ጊዜ ህመማቸውን ለመታከም ያስቻለውን መልካም ዕድል ይዞላቸው የመጣው የጤና መድህን እንደሆነና እንዳቀለለላቸውም ገልጸውልናል፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ በጤና መድህን አገልግሎት አማካኝነት ከጤና ጣቢያ እስከ ሆስፒታል ሄደው መታከም ችለዋል፡፡ የጤና ክትትልም ሆነ ህክምና ማድረግ የጀመሩት ደግሞ የጤና መድህን አባል ከሆኑ በኋላ ነው። ይህ አገልግሎት ብዙ ጊዜ ሲያሰቃያቸው የነበረውን የሀሞት ጠጠር በቀዶ ህክምና ታክመው እንዲድኑ አድርጓቸዋል። የቀዶ ህክምና አድርገውና ከህመማቸው አገግመው እስኪወጡ ድረስ ምንም አይነት ወጪ ሳያወጡ አልጋና መድሀኒትን ጨምሮ ለህክምና የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን አግኝተው መታከም ችለዋል፡፡

ገንዘብ ከኪሳቸው አውጥተው በዚህ ደረጃ ተኝተው መታከም እንደማይችሉ የሚያነሱት ወይዘሮ አምሳል፣ “ይህ እድል ባይፈጠርልኝ ወይ ከህመሜ ጋር እየተሰቃየሁ መኖር አልያም ደግሞ እስካሁን ሞቼ ነበር። ጤና መድህን ህይወቴን ታድጎኛል” ሲሉ የነበረባቸውን የህመም ስቃይ ያስታውሳሉ። በአመት አንድ ጊዜ ከፍለው የተለያየ የጤና አገልግሎት በተለያየ ጊዜ እንዲያገኙ መንግስት እንዲህ አይነት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ መደሰታቸውን እና በወር ለህክምና የሚጠቀሙት የገንዘብ መጠን በአመት ከከፈሉት እንደሚበልጥ አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ የጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ተሾመ የሽሮ ሜዳ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የጤና መድህን መጠቀም ከጀመሩ አንድ ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት ወይዘሮዋ፣ በወቅቱ አገልግሎቱ የሚጠቅም እንደማይመስላቸውና ረጅም ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟሉ እና ደብተር ሳያወጡ እንደቆዩ ይናገራሉ፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጠቃሚ ሆኖ መመልከታቸውን ያነሳሉ፡፡

“ህመም መቼ እንደሚመጣ አይታወቅም። ከዚህ በፊት ታምሜ ወደ ጤና ተቋም ስሄድ ብዙ ወጪ ነበር የማወጣው” የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ድንገት ህመም በሚያጋጥምበት ወቅት የጤና መድህን ደብተር ይዞ ወደ ጤና ጣቢያ የሄደ ሠው ያለምንም ችግር መታከም እንደሚችል ራሳቸውን ማሳያ አድርገው ተናግረዋል፡፡

እንደሳቸው ገለፃ፤ ብዙ ጊዜ በጤና መድህኑ ልጃቸውን አሳክመዋል፡፡ የደም ግፊት ታማሚ በመሆናቸው በየጊዜው እየሄዱ መድሀኒት ይወስዳሉ፡፡ ከጤና ጣቢያ ያለፈ ህመም ሲያጋጥማቸውም እስከ ሆስፒታል ድረስ በሪፈር ተልከው ህክምና አግኝተዋል። በዓመት አንድ ጊዜ ክፍያ ከፍሎ አመቱን ሙሉ ልጃቸውንና ባለቤታቸውን ጨምሮ ሙሉ ቤተሰብ በነጻ ከመታከም እስከ መድሀኒት ማግኘት መቻል ትልቅ ነገር ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጤና መድህን ተጠቃሚ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ተሾመ እና ወጣት ዮሴፍ ደጀኔ

ወጣት ዮሴፍ ደጀኔ፤ በጉለሌ ክፍለ ከተማ መነን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ ሽሮሜዳ ጤና ጣቢያ የጤና መድህን ደብተሩን ለሦስተኛ ጊዜ ለማሳደስ እንደመጣ ነው የነገረን። በዚህ መንገድ ሙሉ ቤተሰቡ እንደሚታከም የሚናገረው ወጣት ዮሴፍ፣ በተለይም ከሦስት ወር በፊት ወላጅ እናቱ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለአንድ ወር ያህል ተኝተው ህክምና ተከታትለው መውጣታቸውን በማስታወስ የአገልግሎቱን ፋይዳ ከፍተኛነት ከምስጋና ጋር ገልፆልናል፡፡

እንደ ወጣቱ ገለጻ፣ እናቱ በታመሙበት ወቅት በግል ለመታከም የቤተሰቡ አቅም አይችልም፤ እጣ ፈንታቸውም ሞት ሊሆን ይችል ነበር፡፡ መንግስት የጤና መድህን ማመቻቸቱ የወላጅ እናቱን ህይወት ታድጎለታል፡፡ የጤና መድህን ከፍሎ መታከም ለማይችሉ ኢኮኖሚያዊ ችግር ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም አሁን ባለው የኑሮ ውድነት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ያቃለለ ነው፡፡ የጤና መድህን አገልግሎት ጠቀሜታው ብዙ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን ህክምና በሚደረግበት ጤና ጣቢያ እና በሆስፒታል ውስጥ የአንዳንድ መድሀኒት አለመገኘት ይከሰታል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው እንዳለባቸውና በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሲዲ 4 ካውንት ለማሰራት እንደመጡ የሚናገሩት ተገልጋይ፣  ጤና መድህን ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሰጣቸው ገልጸዋል። አስተያየት ሰጪያችን በማብራሪያቸው፤ “በጤና መድህን ከመታቀፋችን በፊት ካለኝ ገቢ ላይ የሚያስፈልገኝን መድሀኒት እገዛለሁ፤ ልጀንም አሳክማለሁ፡፡ በተለያየ ጊዜም አልጋ ይዤ ታክሜ አውቃለሁ፡፡ ዛሬ ላይ አይደለም ገንዘብ ከፍሎ በየጊዜው ተመላልሶና አልጋ ይዞ መታከም ይቅርና ካርድ ለማውጣት ከአቅሜ አንጻር ፈታኝ ነው፡፡ ምናልባትም የጤና መድህን ባይኖር ዛሬ ላይ በህይወት ላልኖር እችል ነበር” ብለዋል::

አንዳንድ የመድሀኒት አይነቶችን በጤና መድህን መግዛት እንደማይችሉና በሌላቸው አቅም ገንዘብ ተበድረው ለመግዛት እንደተገደዱ ቅሬታቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪያችን፣ ይህን ችግር መንግስት ተመልክቶ እልባት ቢሰጠው ጥሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደተናገሩት፣ ጤና መድህን ለብዙዎች አጋዥ አቅም ሆኗል፡፡ የገቢ አቅማቸው ሳያስጨንቃቸው የህመም ስሜት ሲሰማቸው በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጋቸው ነው፡፡ እስከ አሁን የተሰሩትን በመቃኘት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ደግሞ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሀንስ ጫላ ዓመታዊ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ምዝገባ በተመለከተ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ፍትሀዊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አንዱ ነው። ጤና ቢሮ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ባለፉት ዓመታት በርካታ ነዋሪዎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ከዚህ አንጻር በ2016 ዓ.ም ብቻ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድህን አባል ሆነው ከመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በድግግሞሽ በተመላላሽና በተኝቶ ህክምና በጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች ባሉ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዮሀንስ፣ በጉዳዩ ዙሪያ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በ2017 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ነባር አባላትን ሙሉ በሙሉ አገልግሎታቸውን እንዲያድሱ በማድረግና ተጨማሪ 10 በመቶ አዳዲስ አባላትን በመጨመር በአጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዟል፡፡ .በዚህም ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 ድረስ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የነባርና አዲሰ አባላት ምዝገባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ መደበኛ የመዋጮ መጠን 1 ሺህ 500 ብር ሲሆን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ አዲስ ለሚዘገቡ ደግሞ መደበኛ መዋጮው ላይ የመመዝገቢያ 200 ብርን ጨምሮ አጠቃላይ 1 ሺህ 700 ብር አመታዊ መዋጮ ይከፍላሉ። እድሜቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ልጆችና በአባሉ ስር ለሚገኙ ለእያንዳንደቸው 750 ብር ይከፈላል፡፡

ህብረተሰቡም ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም በዓመት አንድ ቢሊየን የሚጠጋ ብር ለማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ከተማ አስተዳደሩ ድጎማ እንዳደረገ የገለፁት ላፊው፤ ይህም በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው የማህበረሰብ ክፍል የጤና ፍትሀዊነት ለማስፈን እገዛ አድርጎል። ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ነዋሪዎች በኪሳቸው ገንዘብ ባለመኖሩ ምክንያት ጤናቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅም አስችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አጠቃላይ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የሚሰጡ አገልግሎቶች ከኮስሞቲክስ እና ከተደጋጋሚ የኩላሊት እጥበት በስተቀር የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ጨምሮ ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ ከኩላሊት እጥበት ጋር ተያይዞ አጣዳፊ ሆኖ ሲገኝ እስከ ሶስት ዙር ድረስ የሚሰጥ ሲሆን፤ ከዚህ በላይ ከሆነ ግን በአገልግሎቱ የማይሸፈን መሆኑን ነው ቢሮ ኃላፊው የገለጹት።

አንዳንድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከመድሀኒት ውስንነት ጋር ተያይዞ ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የመድሀኒትና የብር መጠን አልተቀመጠም፡፡ ማንኛውንም ኦፕራሲዮን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሪፈራል ሆስፒታሎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ሁሉ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ ማንኛውም የጤና ባለሙያ መድሀኒት ሲታዘዝ በጀነሪክ ስም (የመድሀኒቶቹ ስም) እንጂ በብራንድ ስም መሆን የለበትም፡፡ ይህንን መድሀኒት ስጡ አትስጡ፣ ይህ መድሀኒት ውድ ነው ርካሽ አይባልም፡፡ በብራንድ ሲለዩ የመድሀኒቶቹ ዋጋ ልዩነታቸው የተራራቀ ነው፡፡ ይህ ሙያዊ ሥነ ምግባር አይደለም፡፡ ከመድሀኒት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ይህ ስለሆነ ማህበረሰቡም ይህንን ሊረዳ ይገባዋል ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ማናጀር አቶ ብርሀኑ አይካ ከመድሀኒት ጋር ተያይዞ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ ለጤና መድህን አባላት በጤና ተቋማት የሚቀርብላቸው መድሀኒት እጥረት ካጋጠመ ወደ ከነማ (በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር የሚተዳደር) መድሀኒት ቤቶች እንዲላኩ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዴ ታካሚዎች የሚታዘዝላቸውን መድሀኒቶች በተለያየ ምክንያት ላያገኙ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ነው ታካሚዎች መድሀኒት አጣን የሚል ቅሬታ የሚያነሱት፡፡

እንደ አጠቃላይ ከህብረተሰቡ አዳጊ ፍላጎት ጋር ተያይዞ የመድሀኒት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን፤ በተለይም የጤና ተደራሽነቱን ለማስፋት ከተማ አስተዳደሩ ከክፍለ ከተሞች ጋር በመነጋገር ማህበረሰብ አቀፍ መድሀኒት ቤቶችን ለማቋቋም እየተሰራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የጤና መድህን አባልነት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን በመገንዘብ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በመምጣት ራሳቸውናና ቤተሰቦቻቸውን በማስመዝገብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቶ ብርሀኑ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በለይላ መሃመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review