የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ ተጠየቀ

You are currently viewing የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ ተጠየቀ

AMN – መጋቢት 4/2017 ዓ.ም

የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እየተወሰዱ ባሉ የሪፎርም እርምጃዎች ዩኒቨርሲቲዎች ወደፊት ምን አይነት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለባቸው የሚያመላክቱ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም የሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች ዩኒቨርሲቲዎችን ለመቀየር እየተሄደበት ያለውን ሁኔታ አውው በዛ ልክ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው፣ የዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች ዩኒቨርሲቲዎች ካላቸው ራዕይና ተልዕኮ አንጻር የሰሯቸውን ሥራዎች በየጊዜው እየገመገሙ የተጠያቂነት ሥርዓትን መዘርጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

በተለይም የትምህርት ዘርፉን በመለወጥ ፍትሃዊ እና ጥራት ያለው ትምህርትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምልመላ፣ መረጣ እና ምደባ፣ የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነፃ የማህበረሰብ አገልግሎት ረቂቅ ሰነድ ለውይይት መነሻነት በከፍተኛ ትምህርት አስተዳደርና መሰረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ቀርቧል፡፡

የቀረቡት ረቂቅ ሰነዶችም በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞች የሚሄዱንበትን አቅጣጫ ህጋዊ መሰረት ለማስያዝ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የቀረበውን ረቂቅ ሰነድ መነሻ በማድረግ የዩኒቭርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review