AMN – ታኅሣሥ 9 /2017 ዓ.ም
ዲጂታላይዜሽን ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካለው ፋይዳ አኳያ የዲጂታል አካታችነትን በሁሉም መስክ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በማህበራዊ መስክ የዲጂታል አካታችነት የተመለከተ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም አጋር አካላት ታድመዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ዲጂታላይዜሽን ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ ዘርፉን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ አካታች የሆነ የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ ማዘጋጀቷን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ፍላጎት መሆኑን በመገንዘብ ሁሉንም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግና ማንም ወደኋላ መቅረት የለበትም በሚል እሳቤ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ በማህበራዊ መስክ የዲጂታል አካታችነትን የተመለከቱ መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
መድረኩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል።