AMN ታሕሣሥ 6/2017 ዓ.ም
የገላን ጉራ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር የዜጎችን በተሟላ መሠረተ ልማት ውስጥ የመኖር መብትን ያረጋገጠ መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በገላን ጉራ የተቀናጀ የመኖርያ መንደርን ጨምሮ በክፍለ ከተማው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
አዲስ አበባ ባለፉት ጊዜያት የነበራት ገፅታ ፕላንን መሠረት ያላደረገ እና መዲናዋን የማይመጥን መሆኑን ያነሡት ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በተከናወኑ ሥራዎች አዲስ አበባን በሚመጥናት ደረጃ ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር የዘመናት ጥያቄ የነበረውን የነዋሪውን የመሠረተ ልማት ጥያቄ መመለስ ስለመቻሉ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባው እና ለካዛንቺስ የልማት ተነሺዎች የተላለፈው የገላን ጉራ የተቀናጀ መንደር የዜጎችን በተሟላ መሠረተ ልማት ውስጥ የመኖር መብትን ያጎናፀፈ እና የተሠራውም መሠረተ ልማት ነዋሪውን ያማከለ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በገላን ጉራ የተቀናጀ የመኖሪያ መንደር ያሉ የልማት ሥራዎችን የጎበኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የመኖሪያ መንደሩ የአሁኑን እና መጪውን ትውልድ የሚያስተሳስር መሠረታዊ የሚባሉ ልማቶችን የሟላ እና ለሰው ልጆች ምቾትን የሚያጎናፅፍ ስለመሆኑ አንሥተዋል።
የከተማን ዕድገት እና ዘመናዊነትን የሚረጋገጠው ዜጎችን መሠረት ባደረገ ልማት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም ማሳያው በአዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ጊዜያት የተከናወኑት ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በራሄል አበበ