የገንዘብ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕከል አድርጎ እየተካሄደ ነው፡- አህመድ ሽዴ

You are currently viewing የገንዘብ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ማዕከል አድርጎ እየተካሄደ ነው፡- አህመድ ሽዴ

AMN- ጥቅምት 18/2017 ዓ.ም

የገንዘብ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የሚመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ 2024 አመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን በተካሄደው የቡድን 7 ሀገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፎ አድርጓል።

በወቅቱ የቡድን-7 አገራት ፕሬዝዳንት በሆነችው ጣልያን የተመራው ስብሰባ ላይ የአፍሪካ አገራት የገንዘብ ሚኒስትሮችን፣ የዓለም-አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የተሳተፉበት ሲሆን፣ እዳ የመክፈል አቅም እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት ዙሪያ ውይይት ማድረጉ ተመልክቷል ።

እንዲሁም በአፍሪካ የመድኃኒት ምርት ልማት የደረሰበት ደረጃ፣ በአረንጓዴ መሰረተ-ልማት እና ጠንካራና አካታች የአቅርቦት ሰንሰለት በሚጠናከርበት ዙሪያም መምከሩ ተገልጿል ።

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የጣልያኑ ገንዘብ ሚኒስትር ላደረጉላቸው ግብዣ አመስግነው በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር ) ስለሚመራውና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል አድርጎ እየተካሄደ ስላለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተሳታፊዎች ገለጻ ማድረጋቸው ተጠቁሟል።

ይኸው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማዘመን እና የኢኮሚውን እድገት ምንጭ ከመንግስት-መር ወደ ግል-መር ኢኮኖሚ በሚያሸጋግር መልኩ የተቃኘ መሆኑን አስረድተዋል።

የሪፎርሙን ዋና ዋና መስኮች የገለጹት አቶ አህመድ የአገር ውስጥ ገቢ፣ አስተማማኝ የገንዘብ አቅም ከመፍጠር አኳያ ምክንያታዊ የመንግስት ወጪን ማስፈን፣ አቅምን ያገናዘበ የብድር አስተዳደር፣ የተዛባ ኢኮኖሚን ከማስተካከል አኳያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ስርአትን ተግባራዊ ማድረግ፣ ተቋማዊ እና የዘርፍ ማዕቀፎችን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሄም የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የስራ እድሎችን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ እና ሌሎች በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት እያደገ ያለውን የፋይናንስ ፍላጎታቸውን በሚመጥን መልኩ የተራዘመና አነስተኛ ወለድ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ስብሰባው ፈጣን መፍትሄ የሚሹ የአፍሪካ የፋይናንስ ተግዳሮቶችን ጨምሮ እያደገ በመጣው ዕዳ ፣ መድሃኒት ማምረት አቅም ማጠናከር አስፈላጊነትን እንዲሁም በአረንጓዴ መሰረተ ልማት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የአፍሪካ አገራትን ዘላቂ እና አስተማማኝ ልማትን ከማረጋገጥ አኳያ በራስ አቅም ሀብት ማሰባሰብን ጨምሮ አፍሪካ መር የሆነ አገራቱ በራሳቸው የሚመሩት የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የኢንቨስትመንት ፕላን እንዲኖራቸው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትብብሩን ማጠናከር ያለበት መሆኑን ተሰብሰቢዎቹ ተስማምተዋል።

ስብሰባውን የቤኒን፣ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ፣ የማላዊ፣ የሞሪሺየስ እና የዛምቢያ ገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የቡድን 7 ሀገራት ገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የቀድሞ፣ የወቅቱ እና የሚቀጥለው የቡድን 20 ፕሬዝዳንት (ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ) ተወካዮች እንዲሁም የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንዉሚ አዴሲና(ዶ/ር)፣ የዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዎርጄቫ እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጄ ባንጋ መካፈላቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review