የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ ምርት እንዲከተል የሚያደርግ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

You are currently viewing የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ ምርት እንዲከተል የሚያደርግ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

AMN-ታህሣሥ 16/2017 ዓ.ም

የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ዘመናዊ ስልተ ምርት እንዲከተል የሚያደረግ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የዜጎችን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ እሳቤዎችን በማመንጨት ገቢራዊ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው።

በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ በሌማት ትሩፋት፣ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ እንዲሁም በኮሪደር ልማት የተጀመሩ ውጥኖች ተግባራዊ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ከተማንና ነዋሪዎቿን በሚመጥን መልኩ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በክልሎችም ተስፋፍቶ የገጠር የኮሪደር ልማትም በስፋት እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የገጠር የኮሪደር ልማት አይነተ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በገጠር የሚኖረው ሰፊ ህዝብ የሀገሪቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን ጠቅሰው በአመራረትና አኗኗር ዘይቤ ግን ችግሮች ስለመኖራቸው አንስተዋል።

በመሆኑም የገጠር ኮሪደር ልማት ገቢራዊ እየተደረገ ያለው አስቸጋሪ የነበረውን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር መሆኑን ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፣ ጓሮውን በዶሮ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት የተትረፈረፈ በማድረግ ዘመናዊና ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማት የተሻለ መሰረተ ልማት በመዘርጋት በገጠርና በከተማ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት የሚያጠብ መሆንም ገልጸዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሮች ደረጃውን የጠበቀ ቤት በመስራት ከባንክ ገንዘብ መበደርና ሃብት መፍጠር የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት “በቁልቁሉማ” መርሃ ግብር የገጠር ቤቶችን የአሰራር ደረጃ እንዲወጣላቸው በማድረግ የቤት ካርታ ባለቤት የሚያደርጋቸውን ህጎች እያወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሩ በግቢው ውስጥ ትራክተርና መኪና የሚያቆምበትን ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ የመፍጠር ሂደት መሆኑን ገልጸው፤ በተበጣጠሰ መንገድ ሲከናወኑ የነበሩ ስራዎችን የማስተሳሰር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ መንግሥት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማስፋት የገጠር ኮሪደር ልማት በሰራባቸው አካባቢዎች ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቁመው የልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review