የጉምሩክ ኮሚሽን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

You are currently viewing የጉምሩክ ኮሚሽን ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

AMN – ጥር 22/2017 ዓ.ም

የጉምሩክ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል፣ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ፣ ከፌደራል ፖሊስ ጸረ ኮንትሮባንድ አባላት፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር እና ከኦሮሚያ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት፤ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሲቲ ዞን ሙሉ ወረዳ ሱመዳዮ ቀበሌ የተከማቸ የኮንትሮባንድ እቃን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የምትገኘው ሱመዳዮ ቀበሌ፤ የኮንትሮባንድ እቃዎች ማከማቻ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማሰራጫ መጋዘኖች መኖራቸውን በተደጋጋሚ ጥናቶች ተረጋግጠዋል፡፡

ጥናቱን መሠረት በማድረግ ጥር 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገ ኦፕሬሽን 1 በሊዮን 16 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች አዳዲስ አልባሳት፣ ልባሽ ጨርቆች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ መድሀኒት፣ ሲጋራ እና ሺሻ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ኦፕሬሽን 18 ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ እንደያዙ በቁጥጥር የዋሉ መሆኑን ገልጸው ቀሪዎቹ የኮንትሮባንድ እቃዎች በጉምሩክ አዋጅ መሰረት መጋዘን በመበርበር የተያዙ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉትን የኮንትሮባንድ እቃዎች በአጠቃላይ በ34 ተሽከርካሪዎች በማጓጓዝ አዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት መጋዘን መግባታቸውንም ኮሚሽነር ደበሌ ተናግረዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኮንትሮባንዲስቶች ላይ የሚወስደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review