የጋራ ትርክት እንዴት እንገንባ?

ብርሃኑ ሌንጂሶ (/) የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በሶሻል አንትሮፖሎጂ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በሶሺዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በማህበራዊ ሳይንስ የልማት ጥናት ሶስተኛ ድግሪያቸውን ኔዘርላንድ ከሚገኘው ራድቡድ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በአምቦ ዩኒቨርሰቲ በሶሺዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በመምህርነትና ተመራማሪነት፣ ኢንተርናሽናል ሊቭስቶክ ሪሰርች ኢንስቲትዩትን ጨምሮ በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት በተመራማሪነትና አማካሪነት ሰርተዋል። በቅርቡም ብሔርተኝነት የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡

ከእኚህ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ጋር ሀገራችንን ወደፊት ለማራመድ የጋራ ትርክት እንዴት መገንባት እንችላለን? ያሉ ፈተናዎች ምንድን ናቸው? የጋራ ትርክት ለመገንባት ምን መሰራት ይኖርበታል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡                        

አዲስ ልሳን፡የሃገረ መንግስት ግንባታ ሂደትና አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ጥብቅ ትስስር እንዳላቸው ይነሳል። ኢትዮጵያም የረጅም ዓመት እድሜ እንዳላት ይታወቃል። በአንፃሩ በሀገራዊ ትርክት ግንባታችን ላይ ጉድለት እንዳለ ይነሳል። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች እንዴት ያይዋቸዋል

የማህበራዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር

ብርሃኑ (/)ትርክት ፅንሰ ሀሳቡ ሰፊ ነው፡፡ ስለምንም ነገር የሚኖረን ግንዛቤና መረዳት የሚመጣው ከትርክት ነው። የሰው ልጅ የትርክት ውጤት ነው፡፡ ስለራሱ መናገር የሚችለውና ሌሎች ያንን ተቀብለው መልሰው ስለእሱ የሚናገሩት የትርክት ውጤት ነው፡፡ ሀገርና ሀገረ መንግስት በህዝቦች የጋራ ስምምነት፣ የጋራ ፍላጎት፣ የጋራ መረዳት ላይ የሚቆም ስለሆነ የጋራ የሆነ ትርክት፣ የጋራ የሆነ አረዳድ፣ ንግርቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው ሀገር ስለራሱ በሚነግረው ንግርት ወይም በሚተርከው ትርክትና ሌሎች እሱን ተቀብለው በሚሰጡት እውቅናና መልሰው በሚተርኩት ልክ ነው። ኃያላን ሀገራት የሚባሉት፣ ኃያልነታቸውን የፈጠሩትና ሌሎች የዓለም ሀገራት ዘንድ ያሰረፁበትን መንገድ ብናይ የትርክታቸው ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ትልቅና ልዕለ ኃያል ተደርጋ እንድትሳል ያደረጋት አንዱ ስለራሳቸው በሆሊውድ ፊልሞቻቸው በሚነገረውና በሚታየው ጭምር ነው፡፡ ትርክት ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ለህዝቦች ስምምነት፣ ለአብሮነት እጅግ መሰረታዊ የሆነ ጉዳይ ነው። የጋራ ትርክት የሚመነጨው ከጋራ ታሪክ፣ ከጋራ ባህል፣ ህዝቡ ከሚጋራቸው የጋራ ምልክቶች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ያለው ሀገረ መንግስት ያላት ብትሆንም የጋራ ትርክት መገንባት ላይ ግን ብዙ አልተሰራም፡፡ ይኽ የመጣው በሀገሪቱ ውስጥ ካለው በርከት ያለ ብዝሃነት ነው፡፡ ብዝሃነት በራሱ የጋራ ትርክት እንዳይኖር ያደርጋል ማለት ሳይሆን ብዝሃነትን ተረድቶ፣ አክብሮና ተቀብሎ የጋራ የሆኑ እሴቶችን በስምምነት መገንባት ላይ የተሰራው አነስተኛ ስለነበር የጋራ ትርክት ገንብተናል ብለን በድፍረት ለመናገር አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡   

አዲስ ልሳን፡የጋራ ሀገራዊ ትርክት እጦት ጉዳቱ እስከምን ድረስ ነው?

ብርሃኑ (/)በጣም ትልቅ ችግር የሚያመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ ላይ እንዳልኩት ሀገር በራሱ የጋራ ትርክት ውጤት ናት፡፡ ሀገር ሲባል በአንድ አካባቢ የሚኖሩ የሚጋሯቸው ነገሮች ያሏቸው፣ የጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ያላቸው ህዝቦች ተስማምተው የሚመሰርቱት የጋራ ቤት ነው። ይህንን ለመመስረት ከምንጠቀምባቸው መሳሪያዎች ትርክት የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል። የጋራ እጣ ፈንታ እንዳለን በትርክቶቻችን፣ በንግርቶቻችን፣ ህዝቡ እንዲስማማበት፣ እንዲቀበልና እንዲሰርፅ ማድረግ መቻል አለብን፡፡ የጋራ ሀገር በመመስረታችን፣ አንድ ላይ በመሆናችን የምናገኘውን ጥቅም በዚያው ልክ ማስረፅ መቻል አለብን፡፡ የጋራ ምልክቶችን ፈጥረን፣ እነዚያን ምልክቶች በጋራ እንድንጋራቸው የምናደርገው በትርክቶቻችን አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በስርዓት አለመገንባታቸውና የጋራ ትርክት ጎልቶ ባለመውጣቱ የሚኖረን ሀገር ደካማ ይሆናል። በህዝቦች ዘንድ የጋራ የሆነ ጠንካራ እይታ ስለማይኖር በልማት ይሁን ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር፣ በምናደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በሌሎች ሀገሮች እንደ ጠንካራ አጋር የመታየት ሁኔታን የሚያቀጭጭ ነው፡፡ የጋራ ትርክት መገንባት ባለመቻላችን መድረስ የሚገባን ቦታ ሳንደርስ ቀርተናል፡፡

አዲስ ልሳን፡እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዝሃ ማንነት ያላቸው ህዝቦች በሚገኙበት ሀገር ሁሉን አቃፊና አሰባሳቢ ትርክት እንዴት ነው መፍጠር የሚቻለው?

ብርሃኑ (/)አንድ ሀገር ሰፊ ብዝሃነት ያለበት ነው ማለት የጋራ የሆነ የሚያስተሳስር ትርክት፣ ማንነት ወይም እሴት ለመፍጠር እንቅፋት ይሆናል ማለት አይደለም። የብዝሃ ባህል፣ የብዝሃ ሃይማኖት፣ የብዝሃ ብሔር ሀገር ብዝሃነቱን መምሰል አለበት ማለት ነው እንጂ ብዝሃነት በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጎረቤት ሀገራት ላይም እንደምናየው አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት ኖሯቸው አንድ ጠንካራ ሀገር መፍጠር ያልቻሉ አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ሀገር ላይ ብዝሃነት የጋራ ትርክት ለመፍጠር እንደ እንቅፋት ተደርጎ የሚታየው ትክክል አይደለም፡፡ ብዝሃነት እንደውም አንድ ላይ ለመምጣትና ለመነጋገር እድል የሚከፍት ነው፡፡ ምክንያቱም የተለያየ እይታ ስለሚኖረን፣ ያንን እይታ ወደ መሀል አምጥተን፣ ተነጋግረን፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ማንነት  ለመገንባት መሰረት ይጥላል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን  ብዝሃነት መቀበል ነው፡፡ እያንዳንዱ ብሔር ያለው ባህል ለኢትዮጵያ ፀጋ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል የተለያየ የብዝሃነት መገለጫ ባላቸው ህዝቦች መካከል የጋራ የሆነ ማንነት ለመፍጠር መስራት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ሀገር ነች፤ ሁሉንም ማንፀባረቅ ባትችል እንኳን ከሁሉም የተውጣጣ እንደ ሀገር የጋራ የሆነ ማንነት መገንባት ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት የተሞከረው የሀገር ግንባታ ችግር የገጠመው የተወሰነውን ብቻ ይዞ ስለሄደ ነው። ስለዚህ የሁሉም ውክልና እንዲኖር ተደርጎ እና ወደ መሀል በመምጣት የጋራ ሀገራዊ ትርክት መገንባት ይቻላል፡፡ ለዚህም የመነጋገሪያና የመወያያ መድረክ ያስፈልጋል፡፡ ሀገራዊ የምክክር መድረክ አንደኛው መንገድ ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡እንደ ዓድዋ፣ ካራማራ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስጠበቅ በጋራ መስዋዕትነት የከፈሉባቸው ድሎች ለታላቅ ትርክት ግንባታ እርሾ ይሆናሉ እየተባለ ይነሳል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ብርሃኑ (/)አዎ፤ እነዚህ ለጋራ ትርክት ግንባታ እርሾ መሆን ይችላሉ፡፡ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእነዚህ ትግሎችና ድሎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ‘የጋራ መስዋዕትነት ከፍለን ሀገርን አስጠብቀናል’ የሚለው ለጋራ ትርክት ግንባታ አንድ ጥሩ መነሻ መሆን ይችላል። ይህንን አንዳንድ ጊዜ ለፖለቲካ ፍጆታ ታሪኩን አጣምሞ የማቅረብ ሁኔታም አለ፡፡ የጋራ ትርክት ወይም ማንነት ለመገንባት እውነታው መኖሩ ብቻ ሳይሆን እውነታው ላይ ስምምነት መድረስ ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ኤርነስት ሬነን የተባለ ፈረንሳዊ የታሪክ ምሁር እንደሚለው፣ ‘ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በሁለት ምሰሶዎች ላይ ነው፡፡ አንድም በአንድ ሀገር የሚኖሩ ህዝቦች አብረው ለመስራት በሚወስኑት ነገር ላይ ነው፡፡ ሌላኛው ህዝቦች ታሪካቸውን በጋራ አስታውሰው አብረው ወደፊት ለመኖር ቃል ኪዳን በሚገቡበት ጉዳይ ላይ ነው፡፡’ ባለፈው ታሪካችን ውስጥ መርሳት ያለብንን በጋራ ተስማምተን ለመርሳት፣ በጋራ ልናስታውስ የሚገቡንን በጋራ ለማስታወስ እና አብረን ለመገንባት ቁርጠኝነት ካለን ጠንካራ ሀገር መገንባት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረች፣ ከጠላት የተቃጣባትን ወረራ የመከተች፣ አሁን ህዝቧ እንዲህ ዓይነት ነገር ያላቸው፣ ወደፊት አብሮ ለመልማትና ለመበልፀግ፣ የጋራ ሰላማቸውን ለማስጠበቅ የወሰኑ ወዘተ. እየተባለ የሀገሪቷን ፍላጎትና ርዕይ የሚናገር መሆን አለበት፡፡  ‘ከዚህ በፊት ለጋራ ትርክት የሚሆኑ እርሾዎች  የለንም’ የሚለው ላለውም ዋጋ የማይሰጥ ስለሆነ አያስኬድም፤ ‘ከዚህ በፊት የነበረን ታሪክም አልጋ በአልጋ ነው፤ ሁሉም በደስታ የኖረበት ነው’ የሚለውም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የጋራ የሆኑ የሚያስተሳስሩ ብለን የምንወስዳቸው ታሪኮች አሉ፤ እንደዚሁም የተበዳይነት ስሜትን የፈጠሩ ታሪኮች አሉ፡፡ ሁሉንም በሚዛን በማየት፣ የሚጠቅሙንን ይዘን ወደፊት ለመሄድና በጋራ ለመስራት መስማማት አስፈላጊ ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡በወል ትርክት ግንባታ ላይ ምሁራን ሚናቸውን ከመወጣት አንጻር ያደረጉትን አበርክቶ እንዴት ያዩታል?

ብርሃኑ (/)ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚሞክሩ ምሁራን አሉ፡፡ በሌላ በኩል የምሁርነት ካባን ለብሰው ለወጡበት ብሔር፣ ሃይማኖት፣ አካባቢ ብቻ ወግነው የሚሰሩ አሉ፡፡ ይህ የሚያመጣው ጣጣ ቀላል አይደለም። ብዙ ሰውን በማታለል  ወደ አላስፈላጊ  መንገድ    እንዲያመራ     ያደርጋል። ኢትዮጵያ በሚያስፈልጋት ልክ ምሁራን ነበራት ወይም ምሁራን በሚፈለገው ልክ ገለልተኛ ሆነው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ለሀገራቸው እያበረከቱ ነው የሚለውን ደፍሮ ለመናገር ቢያስቸግርም ጥረት የሚያደርጉ አሉ፡፡

ምሁራን ለትርክት የሚሆን እውነት፣ መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ነው የሚጠበቅባቸው። በእውነት የተገራ ጠንካራ ትርክት ከሆነ ዘላቂና ህዝቦችን የማስማማት እድሉ ከፍተኛ ይሆናል። በየሰፈሩ በሚመረቱ በተለይ ባለንበት የድህረ እውነት ዓለም የጋራ የሆነና ጠንካራ ትርክት መገንባት ቀላል አይደለም፡፡ ምሁራን በመረጃና በማስረጃ በመደገፍ ጠንካራ የወል ትርክት እንዲፈጠር መስራት አለባቸው፡፡      

የታሪክ ምሁራን ሳይወግኑ ታሪካዊ እውነታዎችን ሳይጨምሩ፣ ሳይቀንሱና ሳይበርዙ  እንዲታወቅ ነው ሊሰሩ የሚገባው። ህዝቡ መጥፎውንም ሆነ መልካሙን እንዲያውቅና በዚህ ላይ በመቆም የጋራ የሆነ ማንነት እንዲገነባ መርዳት አለባቸው፡፡ ምሁራን እውነታውን በማውጣትና በማሳየት ሀገርን ማዳን አለባቸው።

አዲስ ልሳን፡ሀይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላትን ለወል ትርክት ግንባታ እንዴት ልንጠቀምባቸው እንችላለን?

ብርሃኑ (/)በዓላት ከጀርባቸው የራሳቸው የሆነ ትርክት አላቸው። አንዳንዶቹ ብናጎላቸው ብዙ ህዝብ ማቀፍ የሚችሉ፣ የብዙ ህዝብ መገናኛ፣ የጋራ ማንነት መገለጫ መሆን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የዘመን መለዋጫን በዓል ብናነሳ ኢትዮጵያውያን ሲባሉ የዘመን መለወጫቸው በዚህን ጊዜ የሆነ፣ የዝናቡ ወቅት አልፎ ወደ ብራው በጋራ የሚሸጋገሩበት ቀን ነው፡፡ እርግጥ በመስከረም ወር አዲስ ዓመት ብቻ ሳይሆን ኢሬቻና ሌሎች በዓላት ይከበራሉ፡፡ እነዚህ በተለያየ ባህልና ቋንቋ ባላቸው ህዝቦች የሚከበሩ ቢሆንም ከልዩነት ይልቅ የወቅት ሽግግርን የሚያሳዩ በመሆናቸውና የጋራ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ስላለ፣ በደንብ ማጉላትና የጋራ ተደርገው እንዲታዩ መስራት ይቻላል፡፡

አዲስ ልሳን፡አዲስ አበባን ለመለወጥና ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደ ከተማ ምን ዓይነት ትርክት ያስፈልጋል?

ብርሃኑ (/)አዲስ አበባ በኢትዮጵያ ትልቋ ከተማ ናት፡፡ አሁን ላይ በእጅጉ እየዘመነችና እየተዋበች መጥታለች፡፡ ከተሜነት የራሱ የሆነ ትርክት አለው፡፡ በገጠር ከሚኖረው ማህበረሰብ ልዩ የሚያደርገው በጣም ብዙ እውነታዎች፣ እውነታ ላይ ተቆሞ የሚነገሩ ትርክቶችና ንግርቶች አሉት። ከተሜነት ሲጀመር የብዝሃነት መገለጫ ነው። የማይተዋወቁ፣ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች ጎረቤት ሆነው አብረው የሚኖሩበት የኑሮ ዘይቤ ያለው የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ነው። ከዚህ አንፃር ልዩነታችንን ጠብቀን የጋራ የሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በመስማማት፣ የአካባቢያችንን ሰላምና ንጽህና በመጠበቅ የምንኖርበት ቦታ ከመሆኑ አንፃር ኑሯችንን የተሻለ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮችን በማጉላት አብሮ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ አዲስ አበባ በብርሃን ፍጥነት በሚባል ደረጃ እየተለወጠች ያለች ከተማ ስለሆነች እሱን በማስቀጠልና በማስፋት እያንዳንዱ የከተማው ነዋሪ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ መረባረብ ይኖርበታል፡፡ ንግግሩ፣ ትርክቱም በዚህ ላይ የሚያጠነጥን እንዲሆን ነው የሚያስፈልገው። የተሻለ ከተማ መፍጠር ለራሳችን የተሻለ ህይወት መፍጠር ነው፡፡ ነዋሪው የራሱን አሻራ በማኖር፣ የተሰራውን ልማት እንደ ራሱ በመጠበቅ፣ ተጨማሪ የልማት ስራዎች እንዲሰሩ በማገዝ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

አዲስ ልሳን፡የወል ትርክት ለመገንባት ሰዎች አስተሳሰብ ላይ አስቀድሞ መሰራት ያለበት ነገር ምንድን ነው?

ብርሃኑ (/)ስለራሳችን እንዲሁም ሌሎች ስለእኛ ያላቸው ግንዛቤ ጭምር የሚመነጨው ስለእኛ ከሚነገረው ትርክት ወይም እኛ ስለራሳችን ከምንናገረው ትርክት ነው፡፡ የምንናገረው ትርክት ደግሞ አሳማኝ መሆን አለበት፡፡ ትርክት ለእያንዳንዱ ነገር ህይወት ወይም ትርጉም ለመስጠት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል።

አንዳንድ ጊዜ ትርክት ሲባል እንደ መጥፎ ነገር ወይም ውሸትና የፈጠራ ወሬ ተደርጎ ይወሰዳል። እዚህ ላይ የጠራ አመለካከት መፍጠር ያስፈልጋል። ለእያንዳንዱ ጉዳይ ትርጉም የሚሰጥ ነው። ለእያንዳንዱ ነገር ትርጉም የሚሰጠው እውነታው ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡ እውነታው ያስፈልጋል፤ ግን እውነታው የሚነገርበት መንገድ ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ጠንካራ ሀገር ለመመስረት የጋራ የሆነ የወል ትርክት መፍጠር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤው ከተፈጠረ በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያውያን እኩል ተቀባይነት ያለው የጋራ ትርክት አብሮ ለመገንባት የሚገነባበትን መንገድ አሳውቆ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዎንታዊ የሆነ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ማስተማር ያስፈልጋል።

አዲስ ልሳን፡ትርክት ግንባታ ላይ ማነው መስራት ያለበት?

ብርሃኑ (/)በተለያየ ደረጃ ነው መሰራት ያለበት፡፡ የሀገራዊ ምክክር መድረክ ለጋራ ትርክት ግንባታ አንድ ትልቅ ዕድል ነው። መገናኛ ብዙሃን፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የሲቪክ ተቋማትና የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጋራ ትርክት መገንባት አስፈላጊነቱ ላይ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ “የእገሌ ብቻ ኃላፊነት ነው” የሚባል አይደለም፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሰሩበት ይገባል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ተመካክረን መጨረሻ ላይ የምንደርስበት መግባባት የጋራ ስለሚሆን ይህንን ሁሉም እንዲገነዘበውና እንዲያውቀው ማድረግ ላይ በሰፊው መስራት ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ልሳን፡በድህረ እውነት ዘመን የወል ትርክት ግንባታ ቀላል አይደለም ብለዋል፡፡ ለጋራ ትርክት ግንባታ ፈተናዎች ምንድን ናቸው?

ብርሃኑ (/)የድህረ እውነት ዘመን (Post Truth Era) እንኳን እንደ እኛ የጋራ ማንነት ወይም እሴት በደንብ ባልገነባች ሀገር፤ የጋራ ነገር አለን፤ በዓለም ዙሪያ ሀያል መሆናችንን አረጋግጠናል ብለው ለሚያምኑ ሀገራትም ፈተና ሆኗል፡፡ ለሁሉም የዓለም ሀገራት የመጣ ፈተና ነው። ለእኛ ግን በተለየ ፈተና እንዳይሆን መስራት አለብን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ በፊትም የጋራ የሚያስተሳስሩን ጉዳዮች ላይ በደንብ ስላልገነባን እንዳያንገዳግደን መስራት አለብን። የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር መድረክ እና ሌሎችንም አማራጮችን ውጤታማ እንዲሆኑ መስራት አለብን፡፡ 

አዲስ ልሳን፡የድህረ እውነት ዘመን ጫናው እንዴት ይገለፃል?

ብርሃኑ (/)ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ያደጉ ሀገራት የመረጃ ማህበረሰብ ነች ባይባልም መረጃ በማምረት፣ በመሸጥ፣ በማዛባት የሚተዳደሩ ሰዎች ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ስለአንድ ነገር የሚኖረው እውነት አንድ ብቻ ነው። ነገር ግን ያንን እውነት የሚሸጡ ሰዎች እየጨመሩ ሲሄዱ ተመሳሳይ እውነት በመሸጥ ገበያ ስለማያገኙ መረጃውን ወደ ማዛባት የሚሄዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ መረጃውን በማጣመም፣ በማሰማመር የተሻለ እንዲሸጥ የሚደረግ ጥረት ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ እናንተ የምትሰሩትን ዜና አንዱ ወስዶ ዩቲዩብ ላይ አጣምሞ ሲሰራ የተሻለ እይታና ተከታይ ሊያገኝ ይችላል፡፡ የተዛበው መረጃ እንደ አለመታደል ሆኖ የተሻለ እየተሸጠ ያለበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በሰዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት፣ በሀገር ደረጃ የሚኖረውን ሰላምና መረጋጋት በእጅጉ የሚበጠብጡ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ባለንበት ዓለም ይህንን በቀላሉ መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የመረጃ ፍሰቱ እንደ ድሮ ከላይ ወደ ታች አይደለም የሚሄደው፡፡ ሰዎች እውነተኛ መረጃን ከውሸት መለየት እንዲችሉ ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ልንቋቋመው የምንችለው ነው። ከዚህ በፊት ብዙ የሚያስማሙን የጋራ ትርክት የለንም እያልን በምናነሳበት ሀገር፣ ይህንን በመለጠጥ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ ሊወስዱ የሚችሉ ችግሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ ይህንን በመረዳት ሰዎች ለሀሰተኛ መረጃ እጅ እንዳይሰጡና እንዲጠነቀቁ በተለይ መደበኛ ሚዲያዎች እውነተኛ መረጃ በማድረስና የውሸት መረጃዎች ሲወጡ በማጋለጥ መስራት አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ወደ አለመረጋጋት ሊወስድ የሚችል አደጋ ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለታላቅ ትርክት ግንባታ ያለው አስተዋፅኦ እንዴት ይገልፁታል?

ብርሃኑ (/)ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅና በኩራት የሚናገሩላቸው ጉዳዮች ሲበዙ የጋራ ትርክት በሂደት እየተፈጠረ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በኩራትና በልበ ሙሉነት ከሚናገሩላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። በዓለም ላይ የምንታወቅበት የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኢትዮጵያዊውያን በኩራት የሚናገሩለት ተቋም ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሌላኛው የኢትዮጵያውያን ኩራት ነው፡፡ የህዳሴ ግድብን ልዩ የሚያደርገው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አቅሙ በፈቀደው ልክ አሻራውን ያሳረፈበት ስለሆነ አንድ የጋራ የሆነ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ የሚናገሩለት ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሚያመጣው ልማት የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ህይወት ላይ የሚኖረው አዎንታዊ ተፅዕኖ በመካከላችን ያለውን ትስስር ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደርሰዋል፡፡ የፕሮጀክቱ በስኬት መጠናቀቅ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚፈጥረው ስሜትና መነሳሳት ሌሎች የጋራ ነገሮችን አብሮ ለመጀመርና የጋራ ትርክት ለመገንባት ጥሩ መነሻ የሚጥል ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን፡፡

ብርሃኑ (/)እኔም ስለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review