AMN – ጥር 6/2017 ዓ.ም
በእስራኤል እና ሐማስ መካከል የሚደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ረቂቅ እና ታጋቾችን የመልቀቅ ጉዳይ ከመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱን ለስምምነቱ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ይህ የተሰማው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደራቸው በጉዳዩ ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ማስታወቃቸውን እና በአሁኑ ሰዓትም ወደ መጨረሻው እና ፍሬ ወደ ማፍራት መቃረቡን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።
የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኘው ስምምነቱ በሰዓታት፣ በቀናት አልያም ከዚያ በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚያገኝ እምነታቸውን አስቀምጠዋል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በትላንትናው ዕለት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያምን ኔታንያሁን እና የኳታሩን ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አልታኒን አነጋግረዋል።
የሐማስ እና እስራኤል ባለሥልጣናትም በአንድ ሕንፃ ውስጥ ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ጥልቀት ያላቸው ቴክኒካዊ ጉዳዮችም ሰፊውን የውይይት ጊዜ ወስዷል ነው የተባለው።

በስምምነቱ የመጀመሪያ ቀን ሐማስ ሦስት ታጋቾችን እንደሚለቅቅ እና እስራኤልም ሕዝብ በብዛት ከሚገኝበት አካባቢዎች ወታደሮችን እንደምታስወጣ መስማማታቸው ተጠቁሟል።
ከስምምነቱ ሰባት ቀናት በኋላ ደግሞ ሐማስ አራት ታጋቾችን ይለቅቃል፤ እስራኤልም በደቡብ በኩል ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ሰሜን እንዲመለሱ ትፈቅዳለች ተብሏል።
መኪናዎች፣ በእንስሳት ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጋሪዎች እና የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎች ደግሞ በግብጽ እና ኳታር የኤክስሬይ ማሽን ቁጥጥር እየተደረገባቸው በጋዛ ሰርጥ በሚገኘው በሳላህ አል-ዲን መንገድ በኩል ብቻ መንቀሰቃስ ይፈቀድላቸዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት የእስራኤል ወታደሮች በፍላደልፊያ ኮሪደር እንዲቆዩ የሚያደርግ እና በሰሜን እና በደቡብ ድንበር መካከል የ800 ሜትር ከጦር ነፃ ቀጣና እንዲኖር ያስችላል።
አንድ ሺህ የፍልስጤም እስረኞችን ለመፍታት እስራኤል የተስማማች ሲሆን ሐማስ በበኩሉ 34 የታገቱ ሰዎችን ይለቅቃል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በተካሄደ በ16ኛው ቀን ላይ 2ኛው እና 3ኛው የስምምነት ምዕራፍ እንደሚጀመር ተገልጿል።

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅነንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን ስምምነቱ በጆ ባይደን የመጨረሻው የፕሬዚዳንትነት ማብቂያ በሆነው በዚህ ሳምንት ሊካሄድ ይችላል ብለዋል።
የተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልእክተኛም በዶሃ በተካሄደው የንግግር መድረክ ላይ መገኘታቸው ተሰምቷል።
ትራምፕ እ.አ.አ ጥር 20/2025 ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከማምራታቸው በፊት ታጋቾች ሊለቀቁ እንደሚገባ መዛታቸው ይታወሳል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር እስካሁን ብዙ መሠራቱን እና ስምምነቱም ከቀደመው ጊዜ ይልቅ አሁን ላይ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ተስፋ ሰጪው ንግግር እየተካሄደ ባለበት ሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 50 ሰዎች ሞተዋል።
ሪፖርቶቸ እንዳመለከቱት ጥቃቱ ትምህርት ቤቶችን፣ መሰብሰቢያ እና መኖሪያ ቤቶችን ኢላማ ያደረገ ነው ተብሏል። በዚሁ ቀን እስራኤል 5 ወታደሮቼ በጋዛ ሰርጥ ተገለውብኛል ማለቷን ቢቢሲ ዘግቧል።
በፈረንጆቹ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ላይ ሐማስ በከፈተው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ወዲያው ሲሞቱ 251 የሚሆኑ ደግሞ ታግተው ወደ ጋዛ ተወስደዋል።
እስራኤልም በአጸፋው ሐማስን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ አካሄደች።
በጦርነቱ ታዲያ እስካሁን ከ46 ሺ 500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ሐማስ መራሹ የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አስታውቋል።
አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ እስራኤል እና ሐማስን ለማደራደር ኃላፊነት የወሰዱ ሀገራት ናቸው።
በማሬ ቃጦ