AMN- ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም
የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በቢሾፋቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የፖሊሲ ማስተዋወቂያ መድረኩ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ይቆያል፡፡
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን (ዶ/ር) ጨምሮ የፌደራል፣የክልል ግብርና ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የግብርና እና ገጠር ልማት የሚመራበት የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ስልቶች ተቀርጸው ስራ ላይ የዋሉት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፖሊሲው ምርታማነትን በማሳደግ፣ ድህነትን በመቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ግብርና የኢኮኖሚ ዕድገት የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ እንዳስቻለው ተገልጿል።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሰረታዊ ዓላማ ፣በግብርና ምርታማነት የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ ዜጎችን በመደገፍ፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትን በማሳደግና የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥርዓትን በመዘርጋት የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን ማሳካት መሆኑ ተገልጿል።
የገጠር መሬት ደንና ተፈጥሮ ሃብት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የቴክኖሎጂ፣ ግብዓት እና አገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት፣ የውሃ አጠቃቀምና አስተዳደር፣ የምርት ግብይትን ማሳለጥ የፖሊሲው ማጠንጠኛ ናቸው፡፡
በተጨማሪም የገጠር ኢኮኖሚ ልማት መሰረተ ልማት፣የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግና ማጠናከር፣የግብርናና ገጠር ልማት ፋይናንስ ሥርዓት፣ተቋማዊ የአሰራር ሥርዓት እንዲሁም የግብርና አካታችነትና ዘላቂነት በፖሊሲው የተመላከቱ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።
ዘላቂ የምርትና ምርታማነት ዕድገት፣ያደገ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን፣ የገጠር ነዋሪዎች ገቢ እና የገጠር መዋቅራዊ ሽግግር፣አካታች የግብርና ገጠር ልማት እንዲሁም ሀገራዊ የምግብ እና የሥነ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚሉት ደግሞ የፖሊሲው ቁልፍ የውጤት መስኮች መሆናቸው ተመላክቷል።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ርዕይ በ2030 ዓ.ም ግብርናን በማሻገር በገጠር መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ለሀገር ብልፅግና ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማስቻል መሆኑም ተጠቁሟል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።