AMN – ጳጉሜን 4/2016 ዓ.ም
የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት በፈጣን የሥራ ሂደት በመሠራት ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ከአዲስ አበባ ምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት በተጨማሪ የጎንደር ከተማን የኮሪደር ልማት ሥራ እየደገፉ ያሉት ከንቲባ አዳነች በጎንደር ከተማ በመገኘት የኮሪደር ልማቱን የሥራ ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከጎንደር አውሮፕላን ማረፊያ እስከ መሐል ከተማ ፒያሳ እና የፋሲል ግንብ ዙሪያ የሚካሄደው የኮሪደር ልማት ከታሰበው በላይ በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን መመልከታቸውን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች፣ ፕሮጀክቱ የከተማው ነዋሪ በሰጠው ድጋፍ በተቀመጠለት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።
በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ የሚካሄደው የኮሪደር ልማት እንደ አዲስ አበባው ሁሉ በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን እና ጥንታዊ ሕንፃዎችን በማስዋብ እና በማልማት የከተማዋን የቱሪስት መስህብነት የበለጠ በሚያሳድግ መልኩ እንደሚካሄድም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሞያዎችን በመመደብ ጭምር ለጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በሰብስቤ ባዩ