AMN – ጥር 24/2017 ዓ.ም
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ሃሳቦች ስራ ላይ ማዋል ከተቻለ የበለጸገች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ ሲሉ የቱርክ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባዔው መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚበጅ እና ቁም ነገር የያዘ ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያነሷቸውን ሀሳቦች መሬት ላይ በማውረድ መተግበር ከተቻለ አይደለም የኢትዮጵያን የአፍሪካን ብልጽግና እውን ማድረግ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም ከኢትዮጵያ አልፎ ለተቀረው ዓለም የሚበጁ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከዓለም ስልጣኔ ጀማሪዎች ቀደምት መሆኗን አመልክተው በተለይም በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዳላት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በባህል፣ በታሪክ፣ በእምነት፣ በቋንቋና በቅርሶቿ የበለጸገች አገር መሆኗ ያስታወሱት ተወካዩ ይህቺ ታሪካዊ አገር በዘመናት መካከል ያጋጠሟትን ፈተናዎች በመሻገር እዚህ የደረሰች መሆኗን መስክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች አገር ብቻ ሳትሆን ለሌሎችም የነጻነት ተምሳሌት ሆና የዘለቀች አገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ለሉአላዊነት እና ለነጻነት ጸንቶ መቆም ኢትዮጵያን እና ቱርክን እንደሚያመሳስላቸው የጠቀሱት ተወካዩ አገራቱ በታሪክም የሚያመሳስላቸው በርካታ ጉዳዮች መኖሩን አስረድተዋል፡፡
የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን የተሻገረ መሆኑን ያወሱት ተወካዩ በዚህም በኢንቨስትመንት ፣ በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርት ፣በቴክኖሎጂ እና በሌሎች መስኮች ያላቸው ትብብር እያደገ እና እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ኤኬ ፓርቲ ለኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ትብብሩን ለማጠናከር እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ቱርክ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን በሚለው መርህ መሰረት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለችም ብለዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ

All reactions:
139Masresha Demissie Eshete, Tsehhay Habte and 137 others