የጤና መረጃ

  • Post category:ጤና

የኮሌራ በሽታ መንስኤው እና መከላከያው፡-

ኮሌራ ‹‹ቪብሪዮ ኮሌራ›› በሚባል መርዛማ ባክቴሪያ የሚመጣ የአንጀት ኢንፌክሽን ሲሆን አጣዳፊ ተቅማጥ የሚያስከትል በሽታ እንደሆነ የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም ዙሪያ ከ1 ነጥብ 3 እስከ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች በዓመቱ በኮሌራ በሽታ እንደሚያዙ እና ከእነዚህም መካከል ከ21 ሺ እስከ 143 ሺ የሚደርሱ ሰዎች በዚህ በሽታ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡

መንስኤው፡-

ኮሌራ የሚተላለፈው በኮሌራ ባክቴሪያ የተበከለ ውሃ በመጠጣት ወይም ምግብ በመመገብ ሲሆን የውሃ እጥረት እና የንፅህና ጉድለት ባለባቸው ቦታዎች የመከሰትና የመዛመት እድሉ ሰፊ መሆኑ ነው የሚገለጸው፡፡

ምልክቶቹ፡-

የኮሌራ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ምልክት ሊያሳዩም ላያሳዩም ይችላሉ፡፡

ሆኖም ግን በበሽታው ከተያዙ 10 ሰዎች መካከል አንዱ ከባድ ምልክት ሊያሳይ እንደሚችል የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

አብዛኛዎቹ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች አልፎ አልፎ የሆድ ቁርጠት ቢኖራቸውም ትኩሳት ግን አይስተዋልባቸውም፡፡

አንድ ሰው የተበከለ ምግብ ከበላ ወይም ውኃ ከጠጣ በኋላ በኮሌራ በሽታ መያዙን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ለማሳየት ከ12 ሰዓት እስከ 5 ቀናት እንደሚወስድ የጤና ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡

በኮሌራ በሽታ የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች በዋናነት ተቅማጥ እና ማስመለስ ሲሆኑ፤ ከባድ የሆነ የኮሌራ ህመም የያዛቸው ሰዎች ግን መጥፎ ጠረን ያለውና የ”ሩዝ ውሃ” የመሰለ ተቅማጥ እንደሚኖረው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል፡፡

መከላከያው(ህክምናው)፡-

በኮሌራ በሽታ የተያዘ ሰው ተቅማጡና ማስመለሱ ቀጣይነት ያለው ከሆነ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ፈሳሽ መሟጠጥ፣ ልብ በፍጥነት መምታት፣ ዝቅተኛ የደም ግፊት መከሰት፣ የኩላሊት መጎዳት፣ ያለመነቃቃት ብሎም ሞት ሊያስከትልበት ይችላል፡፡

ስለዚህ አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ የህክምና እርዳታ እስኪያገኝ ድረስ ከሰውነቱ የሚወጣውን ፈሳሽ ሊተካ የሚችል ፈሳሽ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ሆኖም ግን የኮሌራ በሽታን በዋናነት በላብራቶሪ በሚደረግ የሰገራ ምርመራ ነው መለየት የሚቻለው፡፡

ኮሌራ በልጆችም ሆነ በአዋቂዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ በሽታ ከመሆኑም በላይ፣ በበሽታው የተያዙና ከፍተኛ ተቅማጥ ያለባቸው ሰዎች ሕክምና ካልተደረገላቸው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።

ነገር ግን ቶሎ ሕክምና ከተደረገላቸው አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ ጉዳት ሳያስከትልባቸው ከበሽታው መዳን እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡

በተጨማሪም በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በደም ስር በሚሰጡ ፈሳሾች የህክምና እርደታ የሚከናወን ሲሆን፤ ከባድ ምልክት ላለባቸው ሰዎች ፀረ-ባክቴሪያ መድሀኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ።

ሌላው የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች መካከል ምግብ ከማብሰል እና ልጆችን ከመመገብ በፊት፣ ሽንት ቤት ከተጠቀሙ በኋላ፣ የታመመን ሰው ከተንከባከቡ ወይም ከነኩ በኋላ እጅን በንጹህ ውሃና በሳሙና መታጠብ ይገባል፡፡

በተጨማሪም ለመጠጥ የሚውል ውሃ ደህንነቱ የተጠበቀ ካልሆነ በውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች አክሞ መጠቀም ተገቢነት ያለው ሲሆን፤ ያልበሰሉ ምግቦችን ከመመገብ ይልቅ አብሰሎና በትኩሱ መመገብ በሽታውን ለመከላከከል እንደሚቻል የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

በመጨረሻም የሽንት ቤት ንፅህናን መጠበቅ ባክቴሪያው እንዳይሰራጭ እና ውኃንና ምግብን እንዳይበክል ለማድረግ እንደሚያግዝ ነው የዓለም የጤና መረጃ የሚያመላክተው፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review