AMN – የካቲት 26/2017 ዓ.ም
የጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ በዲጂታል ክፍያ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ከተለያዩ ባንኮች እና የክፍያ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የተቋማቱ ሃላፊዎች ተፈራርመዋል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በአዲስ አበባ እና ድሬደዋ ከተሞች በሙከራ ደረጃ የሚተገበር ሲሆን፣ በቀጣይም ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚሰፋ ነው።

ስምምነቱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊ ለማድረግ እና የፋይናንስ ስርዓቱን በዲጂታል ለመደገፍ የተሰሩ ስራዎችን የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህም ለኅብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የካርድ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ማድረግ እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩም መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።