የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከግሎባል ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ጋር በጤና ፋይናንስ እና በሽታ መከላከል ዙሪያ ተወያዩ

You are currently viewing የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከግሎባል ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ጋር በጤና ፋይናንስ እና በሽታ መከላከል ዙሪያ ተወያዩ

AMN – የካቲት 8/2017 ዓ.ም

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በግሎባል ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ የተመራ ልኡካን ቡድን ጋር የጤና ፋይናንስ እና በሽታ መከላከል ዙሪያ ተወያዩ፡፡

በቅርቡ የተከሰተው የዩስኤይድ ድጋፍ ማቋረጥ ለአፍሪካ ሀገራት የማንቂያ ደውል መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ አሁንም በጤናው ዘርፍ ለሚካሄዱ የጤና ፕሮግራም ሥራዎች የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋታል ብለዋል።

ግሎባል ፈንድ ለኢትዮጵያ እያደረገ ስለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ግሎባል ፈንድ በተለይም እንደ ኤችአይቪ፣ ቲቢ፣ እና ወባ ያሉ በሽታዎች መከላከል ላይ ያደረገውን ድጋፍ ያደነቁት ዶክተር መቅደስ፣ የመጀመሪያ ደረጀ የጤና አገልግሎትን እንዲሁም አጠቃላይ የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ግሎባል ፈንድ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የግሎባል ፈንድ ዋና ዳይሬክተር ፒተር ሳንድስ፣ ኢትዮጵያ በአብዛኞቹ የጤና መመዘኛ መስፈርቶች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን ገልጸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራታቸው እንደሚያኮራቸው ተናግረዋል።

ይህ ትብብር ከፍተኛ ውጤት ለማስመዘገብ በማስቻሉ የግሎባል ፈንድ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ለመሆናቸው በማረጋገጫነት መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ሀገራት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው መግባባት ላይ የደረሱበት ጊዜ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያ ለጤና የምትመድበውን በጀት ማሳደጓ ተምሳሌት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን የጤና ፋይናንሲንግ፣ የፈንድ ክፍተቶችን መሸፈን፣ የሃገር ውስጥ ምርትን ማሳደግና በሽታ መከላከል ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review