AMN- ታህሳስ 5/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ ጤና ተቋማት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቀሚ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል ።
የጤና ባለሞያው በማህበር በመደራጀት የቤት እድል ተጠቃሚ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ቢሮ በስር ከሚገኙ ሆስፒታሎች ፣ የክፍለ ከተማ ጤና ፅህፈት ቤት እና ከጤና ጣቢያ ሃላፊዎች ጋር የቤት ተጠቃሚ በሚሆኑበት አተገባበር መመሪያ ላይ ኦረንቴሽን በመስጠት ውይይት አካሂዷል።
ኦረንቴሽኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽን የህብረት ስራ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰማ ሙሉ ያቀረቡ ሲሆን የጤና ባለሞያው በማህበር ተደራጅቶ የቤት እድል ተጠቃሚ የሚሆንበትን እና ተያያዥ ጉዳዮች ሰነድ አቅርበው አብራርተዋል።
በዚህም የጤና ባለሞያዎች የሚፈልጉትን የቤት መጠን በመምረጥ በተደራጁት ማህበር መሰረት የግንባታውን ጠቅላላ ወጪ 30 በመቶ ቅድሚያ በመክፈል ቀሪውን 70 በመቶ ከባንክ ጋር በሚፈጠር የብድር ስምምነት የሚፈፀም መሆኑን እና ከተማ አስተዳደሩ ለተደራጁት ማህበራት የለማ መሬት እንደሚያዘጋጅም አቶ ሰማ በማብራሪያቸው ገልፀዋል።
በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የጤና ባለሞያዎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና ባለሞያውን ጥያቄ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዮሐንስ የመኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሐንጋቱ መሐመድ መንግስት ያመቻቸውን ይህን እድል በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የቢሮው አማካሪ ወይዘሮ ብርቱካን አህመድ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የጤና ባለሞያውን በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት የመኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ይህ እድል እንዳያመልጥ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ እና ኦረንቴሽኑ እና ውይይቱ በየደረጃው እስከ ባለሞያው ድረስ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ እና ቢሮው የጤና ባለሞያውን ጥያቄ በመመልከት የመኖሪያ ቤት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩት ላለው ተግባር ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።