የጥበባዊ ዝግጅቶች ጥቁምታ

You are currently viewing የጥበባዊ ዝግጅቶች ጥቁምታ

ባለፉት ቀናት በመዲናችን የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች  እና አዳዲስ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎችን ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም  መሰል ዝግጅቶች ተሰናድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የስዕል አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍት መረጃዎች፣ የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ  የዝግጅት ክፍላችን እንደሚከተለው አዘጋጅቷል፡፡

መጽሐፍት

“መባያ” መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው።ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ጌቱ ከተለያዩ አንጋፋ ፀሐፍት የቀነጨባቸውን ስራዎች ከራሱ ሥራዎች ጋር በማጣመር ያሰናዳው አዲስ መጽሐፍ  በቅርቡ ለንባብ እንደሚበቃ ተገልጿል፡፡ መጽሐፉ በቅደመ ህትመት ሽያጭ ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን በቅርቡ በአንባቢያን እጅ እንደሚደርስ ተነግሯል።

በሌላ መረጃ “መንታ ነፍስ” የግጥም መድብል ለንባብ በቅቷል፡፡ የመድብሉ ደራሲ መላክ ማሩ ሲሆን፣ ህይወት፣ ፍቅር፣ ማህበራዊ ጉዳይና ሌሎችንም ሀሳቦቹንና አስተውሎቶቹን በአጠቃላይ የሰው ልጅ ኑረት ላይ የሚያጠነጥኑ ስራዎችን አካትቶባቸዋል ተብሏል፡፡

እንዲሁም  የወዳጄነህ መሐረነ (ዶ/ር) መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ መሆኑ ተነግሯል። በወዳጄነህ “101 የጥበብ ጠብታዎች” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው አዲስ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ ሊበቃ እንደሆነ ተሰምቷል። ወዳጄነህ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ከሶስት በላይ መጻሕፍትን ለንባብ  አብቅቷል፡፡

በሌላ ዜና “መኮንን ሸገኔ የሀገር ባለውለታ” የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬ ተመርቆ ለንባብ እንደሚበቃ ተገልጿል። መጽሐፉ የተዘጋጀው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን አራት ኪሎ  ኢክላስ ህንጻ  በሚገኘው ዋልያ መጽሐፍት መደብር አዳራሽ ተመርቆ ለንባብ ይበቃል። በኦሮሚያ ክልል በባሌ የተወለዱት መኮንን ሸገኔ በመምህርነት ሙያ ሀገራቸውን ያገለገሉና እውቅናን ያተረፉ ሰው ናቸው፡፡

የኪነ-ጥበብ ውይይት

“አውደ ፋጎስ” የኪነ-ጥበብ የውይይት መድረክ  ነገ ይካሄዳል፡፡ ውይይቱ በአሁኑ ጊዜ  62ኛው ዙር  ላይ ደርሷል። እንደ ኤቨንት አዲስ ዘገባ በዚህኛው ገጣሚ ውብአረጋ አድምጥ “አገባባዊ ድጋሞ በጋሽ ሰይፉ መታፈሪያ ግጥሞች እና ነገረ ባይራ” በሚል ርዕስ መነሻ ሀሳብ ያቀርባል። ይህ ውይይት ከቀኑ 8:00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አግልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።

ስእል

በእይታ ላይ የሚገኘው “የተሸመኑ ትውስታዎች” የሥዕል አውደ ርዕይ ሊጠናቀቅ አራት ቀናት ቀርተውታል፡፡ በወጣቱ ሠዓሊ ብርሃኑ ማናዬ የተዘጋጁ ሥዕሎች የቀረቡበት የሥዕል አውደ ርዕዩ ከባለፈው ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖስታ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በሚገኘው “The Space Ethiopia” የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ እየበቃ ይገኛል። በዳግም አበበ አጋፋሪነት የተዘጋጀው ይህ አውደ ርዕይ የተለያዩ የስዕል አቀራረቦችን እንዲሁም በተለያዩ የአሳሳል ዘይቤ የተሰሩ የስዕል አይነቶችን ያካተተ ሲሆን  ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ የቅርብ ሩቅ የተሰኘው ቴአትር በልዩ ሁኔታ ቅዳሜ 8:30 ሰዓት እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች  የተሰኘው ቴአትር በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡ እሁድ በ8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር የሚታይ  ሲሆን  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር ከሚታዩት መካከል ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ የተሰኙ ቴአትሮች ይገኙበታል፡፡

በጊዜው አማረ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review