መሠረታዊ ወታደር ዘላለም ቤዛነህ እና መሰረታዊ ወታደር ዳንኤል ሙሉቀን ይባላሉ።
ሁለቱ ወጣት ወታደሮች ምንም እንኳን የልጅነት መንገዳቸው የተለያየ ቢሆንም በሀገር ፍቅር ማዕበል የተሳሰሩ ጓደኛሞች ናቸው።
ሁለቱ መሠረታዊ ወታደሮች የጀግኖች ልጆች በአባቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው።
የሀገር ፍቅር በደም ስራቸው ገብቶ ለወታደርነት ሙያ ያላቸው ክብር ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያብብ መኖሩን ይናገራሉ።
ሁለቱም የማወቅ ጉጉት የሞላባቸው ማንኛውንም ነገር የመመራመር ፍላጎት ያላቸው ልጆች ናቸው። እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ ማንኛውንም ነገር መነካካት ይወዱ ነበር።
ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው አጠናቀዋል።
በተለይ ዳንኤል በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በውጤት አጠናቋል። ነገር ግን የሀገር ፍቅርና የአባቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ በልባቸው ውስጥ ነግሶ የተማሩበትን እውቀት ለሀገር ክብር ለመጠቀም ወሰኑ።
በአዋሽ አርባ ውጊያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት ለሜካናይዝድ ስልጠና ሲገናኙ የጋራ ፍላጎታቸውና የሀገር ፍቅራቸው ወዲያውኑ አቀራረባቸው።
በማሰልጠኛው ቆይታቸውም ከመደበኛ ስልጠናቸው ጎን ለጎን የቴክኒክ ችሎታቸውን በማጣመር የጦር መሳሪያ ማስተኮሻ ሶፍትዌር አበለፀጉ ይህንንም ፈጠራ ለመሪዎቻቸው አቀረቡ ውጤታማነቱም ተረጋገጠ።
ይህ ሶፍት ዌር ለማሰልጠኛውም ለተቋሙም ትልቅ የፈጠራ ውጤት እንደሆነ የታመነበት ሲሆን ሁለቱንም በጀግንነታቸውና በፈጠራ ችሎታቸው ላበረከቱት አስተዋፅኦ በምረቃ ስነ-ስርዓታቸው ዕለት የሙሉ አስር አለቅነት ማዕረግ ከጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተበርክቶላቸዋል።
እነዚህ ወጣት አሥር አለቆች የቴክኖሎጂ እውቀትንና የሀገር ፍቅርን በማጣመር ለአገራቸው እድገት አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚቻል በማሳየት አርአያነት ያለው ተግባር ለመከወን ችለዋል።
አሥር አለቃ ዘላለም ቤዛነህ እና አሥር አለቃ ዳንኤል ሙሉቀን የተሰጠን ማዕረግ ከእድገቱ በተጨማሪ ከባድ ሀገራዊ ሀላፊነት በመሆኑ ለበለጠ የፈጠራ ስራ እንተጋለን ሲሉ አጫውተውናል።
ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነዉ መረጃ እንደሚያመላክተዉ አሥር አለቆቹ በጀግንነታቸው፣ በፈጠራ ችሎታቸውና በጓደኝነታቸው የሚታወሱ ለወጣት የሠራዊት አባላትም አርአያነት ያለው ተግባር የሰሩና ተቋማቸዉኝም የዕውቀት ማዕከል እንደሆነ ያመላከቱ ጀግኖች ሆነዋል።