በምህረቱ ፈቃደ
መውጣት መውረድ፣ መውደቅ መነሳት፣ መክሰር ማትረፍ… የሕይወት መልኮች ምን አልባትም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ከገዘፈ ችግር ጋር ተላትመው ቢንገዳገዱ እንጂ የማይወድቁ። አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ወገብ የሚሰብር አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው የመጪውን ተስፋ ስንቅ አድርገው የሚሻገሩ፡፡ አንዳንድ ሰዎች አሉ፤ ጉልበትን ብርክ የሚያስይዝ ፈተና ገጥሟቸው ምትሃት በሚመስል መልኩ አልፈው ህልማቸውን እውን የሚያደርጉ…፡፡ ለዚህ ሁነኛ አስረጂ ይሆናል ያልነውን የሳቦም ከማል ቃሲምን የህይወት መንገድ በአጭር ለማስቃኘት ወድደናል፡፡
ከማል የተወለደው ጎንደር ከተማ ሲሆን ያደገው ደግሞ ደቡብ ጎንደር ወረታ በምትባል አነስ ያለች ከተማ ነው።
ፈተና አንድ
ገና በሦስት ዓመቱ ጠቋሚ ጣቱ ማሽን ውስጥ ገብቶ ተቆርጧል፡፡ ቀጥሎም ተበላሽቶ በቆመ ታንክ ላይ ከጓደኞቹ ጋር አፈሙዙን እያሽከረከረ ሲጫወት የቀኝ እግሩ ተንሸራትቶ ገብቶ መሰል ጉዳት አስተናግዷል። ይህ እንደ እኩዮቹ ጭቃ እንዳያቦካ፣ ውሃ እንዳይራጭ፣ አባሮሽ፣ አኩኩሉ፣ ሌባና ፖሊስ… እንደ ልቡ እንዳይጫወት አድርጎታል፡፡ በሚኖርበት አካባቢ ሌላ አካል ጉዳተኛ አለመኖሩ እና ማህበረሰቡ ለእንደነዚህ አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች ያለው አመለካከት አናሳ መሆኑ ህይወትን ከባድ እንዳደረገበት አብራርቷል፡፡
ፈተና ሁለት
ህይወት ላዘጋጀችለት ፈተና በቀላሉ እጅ የማይሰጠው ከማል፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በወረታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከታተል ጀመረ፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ ወላጆቹ (እናትና አባቱ) ባለመግባባት ምክንያት ፍቺ ፈጸሙ፡፡ ይህ ደግሞ ለተወሰኑ ዓመታት በአባቱ እና እንጀራ እናቱ እጅ እንዲያድግ አደረገው፡፡ ይህ ከአካል ጉዳቱ ባለፈ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ፈጠረበት፡፡ ትምህርቱን እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተከታተለ በኋላ ወላጅ እናቱ ወደሚኖሩበት ጎንደር ከተማ ለመሄድ ተገደደ፡፡
ፈተና ሦስት
ከወላጅ እናቱ ጋር ለመኖር ወስኖ ወደ ጎንደር ሲሄድ ሌላ ፈተና መጋፈጥ ግድ የሚል ሁኔታ ተፈጠረ፤ የኢኮኖሚ ጫና። እናቱ፣ አይደለም እሱን የሚጨምር ራሳቸውን እንኳን በቅጡ የሚያስተዳድር ገቢ አልነበራቸውም። በዚህም በወቅቱ አካል ጉዳተኞችን እና ደጋፊ የሌላቸውን ልጆች የሚያግዝ “ማዘር ትሬዛ” ወደሚባል የእርዳታ ድርጅት በመሄድ በየወሩ የሚሰጥ እርዳታ እስከመቀበል ደርሷል፡፡ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም ፋሲለደስ አንደኛ ደረጃ
ትምህርት
ቤት በመግባት ትምህርቱን ካቆመበት ቀጠለ፡፡
ሆኖም እየገጠሙት ያሉት ውጣ ውረዶች በቀለም ትምህርቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደራቸው አልቀረም። ስምንተኛ ክፍል ላይ የሚሰጠውን ክልል አቀፍ ፈተና ማለፍ ሳይችል ቀረ። ዳግም ተፈትኖ ለማለፍ ያደረገው ጥረት ደግሞ ሰው ሰራሽ እግር ለማስገጠም ወደ ደሴ በመሄዱ ምክንያት ስለተቋረጠ መቀጠል የቻለው በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት አፄ በካፋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ትምህርቱን በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተከታትሏል፡፡ በዚህ ጊዜ የክፍል ጓደኛው ወደሚሰራበት የቴኳንዶ ስፖርት ቤት ይዞት ሄደ፡፡ ይህም የቴኳንዶ ህይወቱ “ሀ” ብሎ እንዲጀመር በር ከፈተ፡፡
ጓደኛው ይሰራበት የነበረው ስፖርት ቤት የፊዚዮ ቴራፒ ባለሙያና የቴኳንዶ አሰልጣኝ አሁን ላይ ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፊዚዮ ቴራፒ መምህርነት እያገለገለ ያለው ሳቦም ቴዎድሮስ ምህረት መሆኑን የሚናገረው ከማል፣ “ስለአካል ጉዳተኝነት ከሌላው ማህበረሰብ የተሻለ ግንዛቤ ነበረው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ጓደኛዬ ወደ ስፖርት ቤቱ ይዞኝ ሄዶ የቴኳንዶ
እንቅስቃሴውን ከተከታተልኩ በኋላ አሰልጣኙ ስልጠናውን እንዴት እንዳገኘነው እኔን ጨምሮ የታደምን ሰዎችን ጠየቀን፡፡ በወቅቱ ለጥያቄው የሰጠሁት ምላሽ ‘እግር ቢኖረኝ እሰራ ነበር’ የሚል ነበር፡፡ እሱም ‘ስለክፍያው እንዳትጨነቅ፤ ነገውኑ ጀምረህ መስራት ትችላለህ’ አለኝ” ሲል ትውስታውን አብራርቶልናል፡፡
ፈተና አራት
በደረሰበት የአካል ጉዳት ምክንያት ስፖርት የመስራት ህልም ያልነበረው ከማል፤ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ ወደ ሌላ የሕይወት መስመር ውስጥ በአንዴ ዘው ብሎ ገባ። ስፖርቱን ሲጀምር መውደቅ፣ መጎዳት ስለነበረው፤ በሚኖርበት አካባቢ ያሉ ሰዎችም “አርፈህ ቁጭበል፤ ምን ያደርግልሃል፤ አትሰራበት” የሚል አስተያየት ይሰጡ ስለነበር በብርቱ ተፈተነ። የወላጅ እናቱ ድጋፍ እና ለስራው ያሳዩት ቀናኢነት የሞራል ስንቅ እንደሆነው ገልጾልናል፡፡
ፈተና አምስት
ፈተና እያበረታው የመጣው ከማል
በስፖርቱ ጅማሮ ላይ አጋጥሞት
የነበረውን ችግር በጥንካሬ አልፎ በ2001 ዓ.ም በቴኳንዶ የመጀመሪያ ዳን
(ዲግሪ) ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ
መሄድ ግድ ይል ነበር። ይህ ለከማል ሌላ ራስ ምታት ሆነበት። ትራንስፖርትን ጨምሮ በቆይታው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መሸፈን የሚችልበት ገንዘብ አልነበረውም። ነገር ግን እንደሌሎች የፈተና ጊዜያት አሁንም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ አስር ብር የምትሸጥ የድጋፍ ትኬት በማዘጋጀት እንዲገዙት የበርካቶችን በር አንኳኳ። የሰበሰበው ብር አልበቃ ሲለው በወቅቱ የመጣለት ሱቅ ላይ መቀጠር ነበር፤ ለዚህም ነጋዴዎችን ተማጸነ፡፡ ሆኖም “እንዴት ከመኪና እቃ አውርደህ መደርደር ትችላለህ፣ እንዴትስ አንተን ልናዝህ እንችላለን…” የሚሉ ምላሾችን በመስጠት ፊታቸውን አዞሩበት፡፡ ሆኖም አንድ ልበ ቀና ነጋዴ በ300 ብር ደመወዝ ተቀጥሮ እንዲሰራ እድሉን አመቻቸለት። በሚሰራት ሱቅ እቃ (የበረባሶ ጫማ) ከመኪና መቀበልና ሱቅ ላይ የመደርደር፣ ፋክቱር የመጻፍ፣ ብር ባንክ ማስገባትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት የተጣለበትን እምነት በሚገባ ተወጣ። የተሰጠውን ደመወዝ በፊት ካገኛት ገንዘብ ጋር በማድረግም ወደ አዲስ አበባ መምጣትና ህልሙን ማሳካት ቻለ፡፡

ፈተና ስድስት
ከመመረቅ ባለፈ የማስተማር ፍላጎትም ያደረበት ከማል፣ ይህ ከሌላ ፈተና ጋር እንዲላተም አደረገው። “ከማል ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል”ን ከፈተ፡፡ ከዚያም ወረታ እና ፓዊ ስልጠና ሰጥቷል፤ አሁን ላይ ደግሞ በባህር ዳር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በጀመረ አካባቢ ግን ሰልጣኝ ማግኘት የሰማይ ያህል ርቆት ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ እንዴት ነው የሚያሰለጥነን? የሚለውን ለማየት ይመጡ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ብዙ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ይህን ተስፋ ባለመቁረጥ ተጋፍጦ ታሪክ ማድረግ ችሏል፡፡ በ2001 ዓ.ም “ሀ” ብሎየጀመረው የማሰልጠን ስራ አሁን 16 ዓመታት ሆኖታል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችንም በዚህ ስልጠና እንዲያልፉ ማድረግ ችሏል። ራሱን እያሳደገም 4ኛ ዳን ላይ በመድረስ በቴኳንዶ “ሳቦም” የሚል ማዕረግ ላይ መድረስ ችሏል፡፡
ሳቦም ከማል ወረታ ከተማ ማሰልጠን በጀመረበት አካባቢ ተማሪው የሆነው፣ አሁን ላይ ደግሞ ሁለተኛ ዳኑን ይዞ ሦስተኛውን ለማግኘት በዝግጅት ላይ ያለውና የራሱ የቴኳንዶ ትምህርት ቤት የከፈተው ቡ ሳቦም አህመድ ኢብራሂም (ቡ ሳቦም- ማለት አራተኛ ዳን ደርሶ ሳቦም የሚለውን ከማግኘት በፊት የሚሰጥ የስልጠና ደረጃ ነው) ለዝግጅት ክፍላችን ከማልን አስመልክቶ በሰጠን አስተያየት፣ “ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፤ መሰልጠንም እፈልግ ነበር። ሳቦም ከማልም ጎንደር እያለ አባቱን ለመጠየቅ ወረታ ሲመጣ ቴኳንዶ ሲሰራ አየሁ፣ ብቃት እንዳለውም አውቅ ነበር፡፡ ለማሰልጠን ሲመጣ ቅድሚያ የተመዘገብኩት እኔ ነኝ፡፡ አሁን ስፖርቱ ላይ ለደረስኩበት ደረጃ የእሱ አበርክቶ ትልቅ ነው” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ አርሴማ አበበ ትባላለች፡፡ በሳቦም ከማል በመሰልጠን አሁን ላይ ሰማያዊ ቀበቶ ላይ ደርሳለች። “2014 ዓ.ም ክረምት ላይ ቴኳንዶ ስጀምር ብዙም ፍላጎት አልነበረችም። አሰልጣኛችን የአካል ጉዳት ያለበት መሆኑን ሳውቅ ደግሞ ‘እንዴት ችሎ ስፖርቱን ሊያሰለጥነን ይችላል?’ የሚል ስሜት ተፈጥሮብኝ ነበር” የምትለው አርሴማ፣ በሂደት ግን ስፖርቱን እየወደደችው እንደመጣች እና ጥቁር ቀበቶዎችን እስከማግኘት የደረሰ ጉዞ ማድረግ እንደምትፈልግ ገልጻልናለች፡፡
ሳቦም ከማል በአስተያየቱ እንደገለጸው፣ በፈተና በታጀበው የሕይወት ጉዞ እውቅና አልተለየውም። በ2000 ዓ.ም በወቅቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ እጅ “የሚሊኒየሙ ታታሪ ወጣት” የሚል የምስክር ወረቀትና ሜዳሊያ፣ በ2014 ዓ.ም ደግሞ በክራንች ሆኖ ቴኳንዶን በመስራት “4ኛ ዳን መያዝ የቻለ አካል ጉዳተኛ” በሚል የአፍሪካ ድንቃ ድንቅ ሰርተፍኬት ማግኘቱን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡
“ቴ እና ኳን” እጅ እና እግር፤ “ዶ” ደግሞ ጭንቅላት ማለት ነው የሚለው ሳቦም ከማል፣ እሱ “ዶ” ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ልጆችን ኮትኩቶ በመልካም ስነ ምግባር የማሳደግ ትልቅ ህልምም አለው፡፡ ለስፖርት ማዕከል ይሆን ዘንድ የባህር ዳር ከተማ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቦታ እንደሰጡት በመግለጽ እውን በማድረግ ረገድ ሌሎች አካላትም ድጋፍ እንዲቸሩት መልዕክቱን አስተላልፏል። እኛም ከሳቦም ከማል የህይወት መንገድ ትምህርት ልንወስድ ይገባል ለማለት እንወዳለን፡፡