AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም
የፅንፈኛው ቡድን ዓላማ ኢትዮጵያ እንድትዳከምና እንድትበታተን የሚፈልጉ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት ማሳካት ነው ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ።
ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በሠራዊቱ የግዳጅ ቀጣና ተገኝተው የሠራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም፣ የተገኙ ድሎችንና በቀጣይ በሚኖሩ ግዳጅና ተልዕኮ ዙሪያ ከሠራዊቱ አመራር ጋር ተወያይተዋል።
ዕዙ የተሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነት እየፈፀመ መሆኑን ያነሱት አዛዡ፤ ዘራፊው ቡድን ከመደራጀት ወደ መበታተን፤ ከፉከራ አንገት ወደ መድፋት ገብቷል ብለዋል፡፡
ይህ የሆነውም በሠራዊታችን ጀግንነት፣ በሠላም ወዳዱ ህዝባችን ድጋፍና በፀጥታ ኃይሉ ቅንጅት ነው ብለዋል።
እኛ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማሰከበር የማንከፍለው መስዋዕትነት የለም ያሉት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በቀጠናው አሁን ለተገኘው አንፃራዊ ሠላም ሠራዊቱ የፈፀማቸው ግዳጅና ተልዕኮ እንዲሁም ያስመዘገባቸው ድሎች ማሳያ እንደሆኑ አንስተዋል።
ፅንፈኛው የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት ለማሳካት ሲል ህዝቡን ለከፋ ችግር ዳርጎታል፤ በዘረፋና በውንብድና ተግባሩም አስፀያፊ ድርጊትን በህዝቡ ላይ ፈፅሟልም ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ በፅንፈኛው ላይ ከሚወስደው የማያዳግም አርምጃ ባሻገር ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራን፣ ከወጣቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በርካታ የሠላም ውይይቶችን በማድረግ ቡድኑ ከህዝቡ እንዲነጠል መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም፤ በርካቶች የሠላም አማራጭን ተቀብለው እንዲገቡ ማስቻሉንና ይህ የሆነውም ሁሉም አመራርና ሠራዊቱ በቅንጅት በመሰራታቸው የተገኘ ውጤት ነው ማለታቸውን የመከላከያ መረጃ ያመለክታል፡፡
አሁን በክልሉና በግዳጅ ቀጠናችን የታየው ሠላምና መረጋጋት የተገኘው ከሕዝቡ ጋር በጥምረት በመስራቱ ነው ያሉት አዛዡ ሕዝቡ ለሠላሙ እየከፈለ ያለው ዋጋ ሠራዊቱን ለበለጠ ድል የሚያነሳሳ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡