የቆሻሻ መሰብሰብ ስራውን ወደ ማታ ለማዘዋወር በትኩረት እየተሰራ ነው
በሰገነት አስማማው
“ከዚህ ቀደም ቆሻሻን ገንዳ ላይ ወስደን ነበር የምንጥለው፡፡ ቶሎ ስለማይነሳም አካባቢያችን መጥፎ ጠረን ነበረው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የፅዳት ባለሙያዎች በሳምንት ሁለት ቀን ቤታችን ድረስ በመምጣት ይሰበስባሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በሌሎች ቀናት ቆሻሻን ካገኙ ያነሳሉ፡፡ በዚህም አካባቢያችን ፅዱ እየሆነ ነው” ሲሉ በጀሞ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ የሆኑት ሳጅን ኪዳኗ አበራ የቤት ለቤት የፅዳት አገልግሎት ጥሩ የሚባል መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ነዋሪዎች ቀኑን ጠብቀው ቆሻሻ የማያወጡ አሉ፡፡ አልፎ አልፎ በየመንገዱ የሚጥሉ አሁንም ይስተዋላሉ የሚሉት ሳጅን ኪዳኗ፣ የፅዳት ባለሙያዎቹ “በተራችሁ አውጡ” ብለው ቢናገሩም ጨለማን ተገን አድርገው የሚጥሉ ስላሉ የሚመለከተው አካል የግንዛቤ ፈጠራውን ማጠናከር አለበት ብለዋል። ከፅዳት ባለሙያዎች ባለፈ በወር አንድ ጊዜ ሁሉም የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ አካባቢውን ያጸዳል፡፡ ከወረዳም ባለሙያዎች በመምጣት ክትትል ያደርጋሉ፡፡ ግንዛቤንም ያስጨብጣሉ፡፡ ይህም በጽዳቱ ላይ የበኩሉን አወንታዊ አስተዋጽኦ በመጫወት ላይ ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ባደግ ጩቃላም የሳጅን ኪዳኗን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ቆሻሻን ገንዳ ላይ በየቀኑ እና በየሰዓቱ ነበር የሚጣለው፡፡ ቆሻሻው እስከ ሳምንት ድረስ ስለማይነሳ አካባቢው ሽታ ነበረው፡፡ አሁን በሳምንት ሶስት ቀን ቤት ለቤት የፅዳት ባለሙያዎች ስለሚሰበስቡ አገልግሎቱ ጥሩ ነው፡፡
“እኔ ቆሻሻን የማስወግደው በመለየት ነው፡፡ ደረቅና ርጥብ ቆሻሻን ለየብቻ አደርጋለሁ፡፡ ጠርሙስና ሃይላንድን ለይቼ ነው የማስወግደው፡፡ አንዳንድ ነዋሪዎች ግን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በደንብ ያልተገነዘቡ አሉ፡፡ ቆሻሻን ሳይለዩ በፌስታል አድርገው መንገድ ላይ የሚጥሉ አሉ፡፡ የፅዳት ባለሙያዎች ግን አይተው አያልፉም፣ ያነሳሉ፡፡ ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ እነሱ ባያፀዱልን ጤናችን አይጠበቅም፤ አካባቢያችንም ፅዱ አይሆንም ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ህብረተሰቡ ሊያግዛቸው ይገባል፡፡ ቆሻሻን በዓይነት በመለየትና በተራ ብቻ በማውጣት የስራቸውን ጫና መቀነስ አለበት” ሲሉ ወይዘሮ ባደግ ተናግረዋል፡፡

የፅዳት ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
የፅዳት ባለሙያዋ ወይዘሮ ብርቄ ብርሃኔ በጀሞ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት አንደኛ በር በሚባለው ብሎክ ቤት ለቤት ቆሻሻን ሲሰበስቡ ነው ያገኘናቸው። ስለስራቸው ሲገልፁ፤ “በዚህ አካባቢ በሳምንት ሶስት ቀን ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ ቤት ለቤት አገልግሎት እሰጣለሁ። ቀድሞ ቆሻሻን ሰብስቤ በመሸከም ወደ ገንዳ ነበር የምወስደው፡፡ አሁን ለውጥ አለ፡፡ ቆሻሻ ቶሎ ቶሎ ይነሳል፡፡ የተሰበሰበው ቆሻሻ በመኪና ነው የሚወሰደው፡፡ ቀኑን ጠብቄ የቤት ለቤት ቆሻሻ ማሰባሰብ አገልግሎት በአግባቡ እየሰጠሁ እገኛለሁ” ብለዋል፡፡
የፅዳት ባለሙያዋ አክለው ሲገልፁ፤ “አብዛኛው ህብረተሰብ የቆሻሻ አወጋገዱ ከበፊቱ እየተሻሻለ መጥቷል። ቀኑን ጠብቆ ቆሻሻን ለይቶ የሚያመጣ አለ። ደረቅና እርጥብ ቆሻሻን ለብቻ በፌስታል ወይም በማዳበሪያ ያደርጋሉ፡፡ እንዲሁም ሃይላንድን ለብቻው ለይተው ያመጣሉ። በተቃራኒው ደግሞ ቆሻሻን የማይለዩና መንገድ ላይ አውጥተው የሚጥሉ ያጋጥማሉ፡፡ ቆሻሻን በመለየት በቀኑ የሚያመጡት ሊመሰገኑ ይገባል። ሌሎችም ቆሻሻን በመለየት በቀኑ ቢያወጡ ለስራችን አጋዥ ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
እኛም በቅኝታችን በዚህ አካባቢ ቤት ለቤት ቆሻሻን የሚሰበስቡ የጽዳት ባለሙያዎች ነዋሪውን በአግባቡ እያገለገሉ እንደሆነ ቃኝተናል፡፡ ነዋሪው የሚያመጣውን ቆሻሻ በአይነት ማለትም ደረቅ ቆሻሻን፣ የፕላስቲክ ቆሻሻን ለብቻ በመለየት በማዳበሪያ አድርገው ወደሚወገድበት ቦታ ለማድረስ የቆሻሻ ማመላለሻ መኪና ሲጠባበቁ ተመልክተናል፡፡
ሌላው የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ቅኝት ያደረገው ቤላ ሰፈር አካባቢ ነው። ወይዘሮ ወይንሸት ገስጥን በዚሁ ሰፈር ጣሊያን ኤምባሲ አካባቢ ቆሻሻን ቤት ለቤት ለሚሰበስቡ የፅዳት ባለሙያዎች ሲሰጡ አገኘናቸው፡፡ “ባለሙያዎቹ በሳምንት ሁለት ቀን ቤታችን ድረስ በመምጣት ቆሻሻ ይሰበስባሉ፡፡ የቆሻሻ አወጋገዱ ከቀድሞ አሁን ለውጥ አለ። እኔም ደረቅ እና የሚበሰብስ ቆሻሻን እንዲሁም ጠርሙስና ፕላስቲክ በመለየት በሶስት ማዳበሪያ ነው የማስቀምጠው፡፡ ቆሻሻ የሚጣልበት ቀን ሲደርስ አውጥቼ እሰጣቸዋለሁ” ሲሉ ቆሻሻን በአግባቡ እንደሚያስወግዱ ገልፀውልናል፡፡
ነዋሪው ቆሻሻን ሲያስወግድ በዓይነት መለየትና ማስቀመጥ አለበት፡፡ የፅዳት ባለሙያዎች እያፀዱ ቆሻሻን በየጊዜው እያነሱልን እኛ ማጥፋት የለብንም፡፡ በመንገድ ላይ ቆሻሻን መጣል የለብንም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ወይዘሮ ሉባባ ኢብራሂምና አቶ ቦጋለ ፍሰሃ በቤላ አካባቢ ከነዋሪዎች ቆሻሻን በመሰብሰብ ወደ መኪና ሲጭኑ ነው ያገኘናቸው፡፡ “ቆሻሻን የምንሰበስበው ቤት ለቤት በመዘዋወር ነው፡፡ ከአንድ ነዋሪ በሳምንት ሁለት ቀን ቆሻሻ እናነሳለን፡፡ ከአንዳንዶች በቀር አብዛኞቹ ነዋሪዎች ቆሻሻን በዓይነት ለይተው ነው የሚያመጡልን፡፡ በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ግንዛቤ ተሻሽሏል፡፡” ብለዋል፡፡
እኛም ነዋሪው በማዳበሪያ ቆሻሻን ለይቶ ሲሰጥና የፅዳት ባለሙያዎቹም በማዳበሪያ በማድረግ በመኪና ጭነው ሲሄዱ ተመልክተናል፡፡
የቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገዱን ለማዘመን ምን እየተሰራ ነው?
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በመዲናዋ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ ምን ደረጃ ላይ ነው? ሲል በአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የአገልግሎት አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሀይሉን አነጋግሯል፡፡ በምላሻቸውም፤ በከተማዋ በአሁኑ ወቅት የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ስርዓትን በመከተል መስራት በመቻሉ አወጋገዱ እየዘመነ መጥቷል። ህብረተሰቡ ቆሻሻን እንደ በፊቱ ገንዳ ድረስ በመሄድ የሚጥል ሳይሆን ቤት ለቤት እንዲወገድለት ስርዓት ተበጅቷል። በከተማዋ ይህን ተግባር የሚያከናውኑ ከ7 ሺህ 300 በላይ አባላት ያሏቸው 125 ማህበራት አሉ፤ ከ194 በላይ ተሽከርካሪ በመጠቀም ቆሻሻን የመሰብሰብና የማስወገድ ስራ ይሰራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ በማህበራቱ ያሉ የፅዳት ባለሙያዎች በተመደቡበት ስፍራ አንድ ነዋሪ ቤት በሳምንት ቢያንስ ሁለት ቀን በመሄድ ቆሻሻ ይሰበስባሉ። ከዚህ በላይ ሶስትና አራት ቀንም ጭምር ይሰራሉ፡፡ ነዋሪው የሚበሰብስና የማይበሰብስ እንዲሁም ፕላስቲክ ቆሻሻን ለብቻ አድርጎ ይጠብቃቸዋል። ለመልሶ መጠቀም የሚውለውን ቆሻሻ በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶች ያስረክባሉ። የተሰበሰበው ቆሻሻ ሽፍን በሆነ ኮምፓክተር መኪና ተጭኖ በከተማዋ ባለው 159 የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ እንዲጓጓዝ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባን አረንጓዴና ፅዱ፣ ዘመናዊ ስማርት ሲቲ በማድረግ ሂደት የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ አብሮ መዘመን ስላለበት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አቶ ግርማ ያነሳሉ፡፡ ይህም ቆሻሻ እንደቀድሞ በገንዳ አይጣልም፡፡ በቀጣይ በከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና ማከማቻ ስፍራዎች እንዲቀንሱ እና ያሉትን የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራዎችን የማዘመን ስራ ይሰራል፡፡ ይህም ህንፃ በመገንባት ለመልሶ መጠቀም የሚሆነውና የማይሆነው ቆሻሻ የሚለይበት፣ የልብስ መቀየሪያ፣ የሻወር አገልግሎት የሚሰጥበት፣ ቢሮ ያካተተ ሆኖ በመገንባት የቆሻሻ አወጋገድን ለማዘመን እየተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም ቆሻሻን ቀን መሰብሰብ ባደጉ ሀገራት ባለው ተሞክሮ አይመከርም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የቆሻሻ መሰብሰብ ስራውን ሙሉ በሙሉ ወደ ማታ ለማዛወር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
አልፎ አልፎ ቆሻሻን በየቦታው የሚጥሉ ነዋሪዎች መኖራቸውን የፅዳት ባለሙያዎቹም ሆኑ ነዋሪዎች ራሳቸው በነገሩን መሰረት የህብረተሰቡ ግንዛቤ ምን ደረጃ ላይ ነው? ላልናቸው ጥያቄ ዳይሬክተሩ ሲመልሱ፤ “ቀድሞ ህብረተሰቡ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ክፍተት ነበረበት፡፡ ኤጀንሲው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በ2015 ዓ.ም ባስጠናው ጥናት መሰረት ህብረተሰቡ ስለ ፅዳት አጠባበቅ ያለው የግንዛቤ ደረጃ 97 በመቶ ነው፡፡ ነገር ግን ያገኘውን ግንዛቤ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ክፍተት እንዳለም ጥናቱ አመላክቷል። ቆሻሻን በየቦታው ከመጣል አንጻር በከተማ ደረጃ እንደትልቅ ችግር ሆኖ ለኛ የደረሰን መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ፕሮግራም ወጥቶ ቤት ለቤት የፅዳት ባለሙያ ቆሻሻን እየሰበሰቡ እያሉ፤ ያለ ፕሮግራም ቆሻሻን አውጥተው መንገድ ላይ የሚጥሉ ካሉ ግንዛቤ ተሰጥቶ ካላስተካከሉ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፡፡ የማይታረሙ ከሆነ በፅዳት ዙሪያ በወጣው ደንብ መሰረት ቅጣት ይጣልባቸዋል” ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው በቀጣይ የግንዛቤ ስራውን የማስፋት፣ የቆሻሻ አወጋገዱን የማዘመን ስራ ማጠናከር፣ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ወደ ሃብት የመቀየር ተግባሩን በትኩረት የሚሰራ ሲሆን የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ በማስቀመጥ አዲስ አበባ ፅዱና ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን አቶ ግርማ ገልፀዋል፡፡
“የመኖሪያ አካባቢ ፅዱ ሲሆን ጤና ይጠበቃል” የሚሉት ዳይሬክተሩ ከዚህ ህብረተሰቡ በየቤቱ የሚያመነጨውን ቆሻሻ በዓይነት በመለየት በሚወገድባቸው ቀናት ብቻ በፕሮግራሙ መሰረት ለፅዳት ባለሙያዎች ማስረከብ ይኖርበታል፡፡ የመኖሪያ ግቢአቸውን እና ከግቢያቸው ውጪ እስከ 5 ሜትር ማፅዳት እንዳለባቸውና በየጊዜው በሚካሄው የፅዳት ንቅናቄ ደግሞ ሁሉም ነዋሪ እየወጣ አካባቢውን ማፅዳት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ “ህብረተሰቡ ቆሻሻን ባልተፈቀደ ቦታ የሚያስቀምጡ አካላት ሲያጋጥመው የማጋለጥ፣ ስለ ቆሻሻ አወጋገድ የማስተማር ስራ መስራት አለበት፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን አዲስ አበባ ፅዱ፣ ውብና ማራኪ፣ ለነዋሪዎቿና ለእንግዶቿ ምቹ የመኖሪያና የስራ አካባቢ እንድትሆን በሚደረገው ርብርብ ነዋሪው በጋራ እንዲሰራ አቶ ግርማ ጥሪ አቅርበዋል፡፡