የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ውስብስብ ወንጀልን የመመርመር ሀገራዊ አቅምን በእጅጉ ከፍ ያደርጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN-ህዳር 7/2017 ዓ.ም

የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ውስብስብ ወንጀልን የመመርመር ሀገራዊ አቅምን በእጅጉ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።

ማዕከሉ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ሲሆን፤ የሰነድ፣ የዘረመል (ዲኤንኤ) ዲጂታል ፎረንሲክ፤ ስውር አሻራና ሌሎች ከፎረንሲክ ጋር የተያያዙ የመርመራና ምርምር ስራዎች የሚከናወኑበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማዕከሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በጸጥታ እና ደህንነት ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ውስብስብ ውንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ የፌዴራል ፖሊስ ይህን መሰረት በማድረግ በቴክኖሎጂ፣ ሰው ሃይልና ተቋማዊ አቅም መደራጀቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም የፌዴራል ፖሊስ ከቴሌኮሙኒኬሽን ውጪ ራሱን የቻለ የተመሰጠረ የኮሙኑኬሽን ስርዓት መዘርጋቱን አውስተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ደግሞ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የኮሙኑኬሽን መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት የፖሊስ ስራ ይበልጥ እንዲደራጅ እያደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የፌዴራል ፖሊስ በተለይ በቴክኖሎጂ ራሱን ለማደራጀት ያከናወናቸው ስራዎች ወንጀል የመከላከል አቅሙ እንዲሻሻል እንዳደረጉትም አብራርተዋል።

ለአብነትም የፌዴራል ፖሊስ የደህንነት ካሜራዎችና የወንጀል መከላከል መተግበሪያዎችን በመጠቀም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የሚሳተፉባቸው የአደባባይ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከል ደግሞ ውስብስብ ወንጀልን የመመርመር ሀገራዊ አቅምን በእጅጉ ከፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

ማዕከሉ እንደ ሀገር ወደ ውጭ ተልኮ ሲከናወን የነበረውን የዘረመል(ዲኤንኤ) ምርመራ ከማስቀረቱም ባሻገር የጎረቤት ሀገራት ጭምር እንዲገለገሉበት ታስቦ መገንባቱንም ጠቅሰዋል።

የፌዴራል ፖሊስ በቀጣይ የቴክኖሎጂ አቅሙን፣ የሰው ኃይል አደረጃጀቱንና ተቋማዊ አቅሙን ለማሳደግ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን እጠናክሮ እንዲቀጥልም ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review