AMN- ጥር 1/2017 ዓ.ም
በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የርዕደ-መሬት ክስተት በተመለከተ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ማካሄዳቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ፡፡
በአስቸኳይ ስብሰባው የሳይንስ ማህበረሰቡ አካላት እና የሁለቱ ክልሎች አመራሮችም መሳተፋቸው ተገልጿል።
ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል በሆኑ አካባቢዎች የተከሰቱ የርዕደ-መሬትና ንዝረት ስጋቶች በልዩ ትኩረት መከታተል የሚገባን መሆኑን ተግባብተናልም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፡፡
የክስተቱ ድግግሞሽ እና ስፋት በአካባቢው በሚኖሩ ዜጎች ላይ ባለው ተፅዕኖ ምክንያት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በማመን በጋራ ግብረ ሀይል የተሰሩ የቅድመ አደጋ መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን መገምገማቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራልና የክልል መዋቅሮች የተቀናጀ የአደጋ ስጋት ምላሽ እየሰጡ መሆኑን እና የሳይንስ ማህበረሰቡ ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተለ መረጃ እየሰጠ መሆኑን አይተናል ሲሉም ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል አጋር አካላት እና የሚመለከታቸው ሴክተሮች የቅድመ መከላከል ስራውን በትኩረት መደገፋቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአስቸኳይ ስብሰባው የርዕደ- መሬት ክስተቶችና የተሰጡ ምላሾችን በዝርዝር በመገምገም በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች እና ተግባራት ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
እስካሁን በቅድመ መከላከል ውጤታማ ስራው ለተሳተፉ አካላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።