የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ3D ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት በዘርፉ እውቅናን ካተረፈው ከኦስትሪያው ግዙፍ የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ባውሚት ግሩፕ ከተባለ እውቅ ኩባንያ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ኦስትሪያ ዎፊንግ ከተማ አቅንተው ከግንባታ ቴክኖሎጂ አቅራቢው ኩባንያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የ3D የኮንስትራክሽን ፕሪንትን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተግባራዊ ለማድረግ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይም ምክክር አድርገዋል፡፡
አቶ ረሻድ ከማል ኮርፖሬሽኑ ለጀመረው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ማስፋትና ማላመድ ስትራቴጂ ትግበራ ተጨማሪ ተሞክሮ ለመቀመር በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተሰናዳው የኮንስትራክሽን ማሽን እና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይም ተሳትፈዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት የአልሙኒየም ፎርምወርክ የግንባታ ቴክኖሎጂን ከኦቪድ ጋር በመሆን ከኮርያ በማስመጣት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ ሲሆን፣ የፕሪካስት የግንባታ ቴክኖሎጂን ከዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግም እየሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡
የአሀኑን ስምምነት ተከትሎ የ3D ኮንስትራክሽን ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂ፣ ኮርፖሬሽኑ ለአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያስተዋወቀው ሦስተኛው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ለመሆን ያስችለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡