የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያከናውኑ የነበረውን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከቡ

You are currently viewing የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያከናውኑ የነበረውን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከቡ

AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሲያከናውኑ የነበረውን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በሰነድ መልክ የተዘጋጀውን የፖለቲካ ፓርቲዎቹን የውይይት ቃለ-ጉባኤ ተረክበዋል።

ሰነዱ በኢትዮጵያ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከታሕሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲደረግ የቆየ የውይይት ቃለ ጉባዔ ሰነድ መሆኑም ተገልጿል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ላለፉት ዓመታት የተካሄደው ውይይት በ8 ዋና ዋና አጀንዳዎችና በ50 ንዑስ አጀንዳዎች ዙሪያ መካሄዱም ተገልጿል።

ሰነዱ ለሀገራዊ ምክክር ሥራዎች በግብዓትነት የሚያገለግል ይሆናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ውይይት ለሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ዕድገት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትም ትልቅ ፋይዳ ያለው ውይይት መሆኑን አንስተው፤ ፓርቲዎች ተቀራርበው ከመከሩ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚቻል አመላክተዋል።

የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት እንደሚችሉም ከውይይቱ መረዳት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች ልዩነቶችን በማክበር በመተባበርና በመደማመጥ ውይይቱን እንዳካሄዱ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውይይቱ ትልቅ ልምድ ማግኘታቸውን ጠቁመው ለዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታም የራሱ ትልቅ ሚና የሚጫወት ውይይት ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በርክክብ መርሃ ግብሩ ለውይይቱ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review