AMN- የካቲት 20/2017 ዓ.ም
የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡና የማለፍ ምጣኔውም ከፍ እንዲል ባለፉት ሶስት ዓመታት የነበሩ ችግሮችን በጥናት በመለየት ችግሩን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት ለተማሪዎች ውጤት መቀነስ ምክንያት የሆኑ ችግሮች በጥናት መለየታቸውን የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከኤ ኤም ኤን ውሎ አዲስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የተማሪዎች የሂሳብና የእንግሊዘኛ እውቀትና ክህሎት ዝቅተኛ መሆን በአጠቃላይ የትምህርት አቀባበላቸውና በፈተና ውጤታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተረጋግጧል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡ ችግሩን ለማስተካከልም ለሁለቱ የትምህርት መስኮች የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
የሶስት ዓመታት የተማሪዎች ውጤት ትንትና ተሰርቶ የተማሪዎች የእውቀት ክፍተት ስለመለየቱ ያብራሩት ዶክተር ዘላለም ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦናም ጭምር እንዲዘጋጁ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የማጠናከሪያ ትምህርትም በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተማሪዎች ስነ ምግባር ላይ በተሰራው ጠንካራ ስራ በራሱ የሚተማመን ትውልድ እየተፈጠረ መምጣቱንና የተሻለ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥርም እያደገ መምጣቱን ዶክተር ዘላለም አስታውቀዋል፡፡
መምህራን ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና ያቀረቡት ቢሮ ሃላፊው ይሄንን ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አደራ ብለዋል፡፡
በካሳሁን አንዱዓለም