የ15ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄደ

You are currently viewing የ15ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄደ

AMN ሰኔ 12/2017

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በክህሎት ውድድር በቴክኖሎጂ በተግባራዊ ጥናትና ምርምር በፋሽን ሾው እንደዚሁም በሁሉም ውድድሮች የአሸናፊዎች አሸናፊ ለሆኑና ለልዩ ተሸላሚዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።

በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሃመድ ልጋኒ ባደረጉት ንግግር በያዝነው አመት የተከበረው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በኮሌጆች የተተገበሩ ጥናትና ምርምሮች የቴክኖሎጂ ውጤቶች የክህሎት ውድድሮችና የመሳሰሉ አመርቂ ውጤቶች ለአውደ ርዕይ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በማጠቃለያ መድረኩም በየደረጃው ላሉ የውድድር አሸናፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ዕውቅና የሚሰጥበት ነው ብለዋል።

15ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በስኬታማነት እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ከየዘርፎቹም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላገኙ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማትና የዕውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ውድድራቸውን በሶስተኛ ደረጃ ላጠናቀቁ የየዘርፍ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው የ30 ሺህ ብር በሁለተኝነት ላጠናቀቁ የ40 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል። ውድድሩን በአንደኝነት ላጠናቀቁም 50 ሺህ ብር እና 106 ሺህ ብር ግምት ያለው ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ሽልማት ተሰጥቷል።

በፋሽን ዲዛይን በአንደኝነት ያጠናቀቀው ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሲሆን የምርታማነት ማሻሻያ ማዕከል ልዩ ተሸላሚ ሆኗል።

የ15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የአሸናፊዎች አሸናፊ የሆኑት 1ኛ ተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ፤ 2ኛ አቃቂ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ እና 3ኛ ምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ሆነዋል።

በዚሁ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ የስራ መመሪያ የሰጡት አቶ ጥራቱ በየነ የቴክኒክና ሙያ ሳምንቱ አሰልጣኞች በአመቱ ውስጥ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ሲያመርቱ የቆዩበትን እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት የተመረቱ የቴክኒክናሙያ ውጤቶች ከገበያው ጋር የሚተሳሰሩበት ነው ብለዋል።

በውድድሩ አሸናፊ የሆናችሁ ኮሌጆችም ለሀገራችሁ ተስፋ በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ይህንን ምቹ ሁኔታ መጠቀም ከአመራሮች ከአሰልጣኞችና ከሰልጣኝም እንደሚጠበቅ ነው ያስገነዘቡት።

በፈጠራና በክህሎት ውድድር አኩሪ ውጤት ያስመዘገቡት ወጣቶች ይበልጥ ቢደገፉ ደግሞ ከዚህም የላቀ መስራት እንደሚችሉ አመላካች ሁኔታዎችን ተመልክተናል። ስለሆነም እንደሀገር ውጤታማ ስኬት ለማስመዝገብ መደጋገፍና ተባብሮ መስራት ይገባናል ብለዋል።

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review