AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቀረቡለት 191 የወንጀል ጉዳዮች እና 167 ከፍታብሔር ጋር የተያያዙ የምርመራ ጥያቄዎችን ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ተቀብሎ በፎረንሲክ ምርመራ በማጣራት 73 በመቶ ሀሰተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተለያዩ የወንጀልና የፍታብሔር ጉዳዮችን በዘመናዊ የፎረንሲክ ምርመራ ላብራቶሪ መሣሪያዎች በሚገባ እየመረመረ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ፎረንሲክ ምርመራ ካደራጃቸው ዘመናዊ የላብራቶሪ ክፍሎች አንዱ የሰነድ ምርመራ ላብራቶሪ መሆኑ ተመላክቷል።
በሰነዶች ላይ የሚፈፀሙ ፊርማዎችን፣ በቲተሮችና በማህተሞች፣ በባንክ ቼኮች፣ በፖስፖርቶች፣ በተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ላይ የተፈፀሙ ድልዝና ስርዞችን፣ በፅሁፎች እና በቁጥሮች እንዲሁም ከውርስ ጋር የተያያዙ ሰነዶችን እና ከቦታ ካርታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመመርመር ትክክለኛ እና ሀሰተኛ መሆናቸውን እያረጋገጠ የፍትሕ ሥርዓቱን በማገዝ የድርሻውን እያበረከተ እንደሚገኝ የፎረንሲክ ምርመራ ዲፓርትመንት ገልጿል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከቀረቡለት 191 የወንጀል ጉዳዮች እና 167 ከፍታብሔር ጋር የተያያዙ የምርመራ ጥያቄዎችን ከፖሊስና ከፍርድ ቤት ተቀብሎ በፎረንሲክ ምርመራ በማጣራት 73 በመቶ ሀሰተኛ መሆናቸውን ማረጋገጡን በማኀበራዊ ትስስር ገፁ አስታውቋል።
ኅብረተሰቡ ማንኛውም ዓይነት ውሎችን ሲዋዋል፣ ኦንላይን ግብይቶች ሲያደርግና ሲፈርም በአጠቃላይ ከሰነድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚገባ ማየትና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል፡፡