AMN-ጥር 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ እና የቻይና 55ኛ ዓመት የወዳጅነት ክብረ በዓል በወዳጅነት አደባባይ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የ55ኛው ዓመት የወዳጅነት ክብረ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየተጠናከረ የመጣውን የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን በመግለጽ የቻይና የንግድ ማህበረሰብ መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ በበኩላቸው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወዳጅነት ጊዜ የማይሽረውና በጊዜ ሂደትም እየተጠናከረ የሚሄድ መሆኑን ተነግረዋል፡፡
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጠ ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እና የቻይና ባህላዊ ትርዒቶች የቀረቡ ሲሆን የዴቦራ ፋውንዴሽንን ለመደገፍ የሚያስችል ባዛርም ተከፍቷል።