AMN – ጥር 2/2017 ዓ.ም
ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቅርቡ የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ ትራምፕ ለውይይት ይፋዊ ጥያቄ አላቀረቡም ማለታቸውን ተከትሎ ነው ዶናልድ ትራምፕ የዛሬውን ይፋዊ መግለጫ ከፍሎሪዳ የሰጡት ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር ሊያደረጉ የሚችሉትን ውይይት በተመለከተ ጥያቄ ማቅረባቸውን በይፋ ባይገልጹም ሁለቱ መሪዎች ግን ስኬታማ የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸው ይታወቃል ።
ትራምፕ በምርጫ አሸናፊነታቸውን ካረጋገጡ በኋላ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እንዳሉት ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ጦርነቱ “በቶሎ ያበቃል” ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል።
ትራምፕ ለጉዳዩ በሰጡት ትኩረት የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩትን እና በአሜሪካ ጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግለው በጡረታ የተገለሉትን ሌተና ጄኔራል ኪት ኬሎግን የዩክሬን እና የሩስያ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሆኑ አቅርበዋል።
ኬሎግ ዩክሬን ተጨማሪ የአሜሪካ እርዳታ እንድታገኝ ከሞስኮ ጋር በሰላም ድርድር ላይ ለመሳተፍ ከተስማማች ብቻ ነው የሚል ሃሳብ አቅርበዋል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውይይቱ እንደሚደረግ ቢገልፁም ስብሰባው መቼ ሊካሄድ እንደሚችል ግን ቀኑን በግልፅ አላስቀመጡም።