AMN – ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም
ጀርመን ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ለሰብዓዊ ተግባራት ለምታደርጋቸው ተግባራት ተገቢውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጀን ሄንፊልድ ገለጹ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እና ከጀርመን የሕዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት የሰብዓዊ ድጋፍ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያና ጀርመን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸው የሰላም ግንባታ ሥራዎች በጥልቀት አብራርተው የጀርመን ድጋፍና አጋርነት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጀን ሄንፊልድ እና ልዑካኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች እንዲሁም ሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዓለም አቀፍ ስደተኞች ተቀብላ በማስተናገድ የምታደርጋቸውን ሰብዓዊ ተግባራትን በማድነቅ ለዚህም ሀገራቸው ተገቢውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡