AMN-የካቲት 12 ቀን 2017 አ.ም
በስፔን ላሊጋ 24ኛ ሳምንት ሪያል ማድሪድ ከኦሳሱና አንድ አቻ የተለያየበትን የቅዳሜ ጨዋታ የመሩት ጆሴ ሊዊስ ሙኑዌራ ሞንቴሮ ከዳኝነት ለጊዜው መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡
የ41 ዓመቱ ጆሴ ሊዊስ ሙኑዌራ ሞንቴሮ ‹‹ቤሊንግሃም ሰድቦኛል›› ብለው በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዳስወጡት ይታወሳል፤ ራሱ ቤሊንግሃም ሆነ ካርሎ አንቸሎቲ የዳኛውን ውሳኔ መቃወማቸው ይታወቃል፡፡
ጣሊያናዊ አሰልጣኝ ካርሊቶ ዳኛው እንግሊዘኛ ቋንቋ መስማት ስለማይችሉ የሰደባቸው መስሏቸው እንጂ ቤሊንግሃም ይህንን አስነዋሪ ድርጊት አልፈጸመም ብለው ከኮከባቸው ጎን መቆማቸው አይዘነጋም፡፡
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እኚህን ሰሞነኛ መነጋገሪያ ዳኛ ከጨዋታ ማገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጆሴ ሊዊስ ሙኑዌራ ሞንቴሮ የታገዱት ከቀይ ካርዱ ጋር በተገናኘ ሳይሆን እንደ አትሌቲኮ ማድሪድ ካሉ ክለቦች ጋር ግንኙነት አለው ከተባለ ‹‹ታለንተስ ስፖርት ካምፓኒ›› ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚጠቁሙ መረጃዎች በመገኘታቸው ነው ተብሏል፡፡
ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ዳኛው ጨዋታዎችን እንዳይመሩ እገዳ የተላለፋባቸው ሲሆን ጥርጣሬው በማስረጃ ከተረጋገጠ ተጨማሪ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ማርካን ጨምሮ በርካታ ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበውታል፡፡
በታምራት አበራ