ጃፓን የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት ትደግፋለች- የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ

You are currently viewing ጃፓን የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት ትደግፋለች- የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ

AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

ጃፓን ለኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ገለጹ።

የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ጋር ተወያይተዋል።

የሽግግር ፍትሕ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር ሴክሬታሪያት ኃላፊ እና የባለሙያዎች ቡድን አባላትም በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጃፓን በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት በጋራ በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመጨረሻ ጊዜ እልባት በመስጠት ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ትግበራ መግባቱን ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ገልጸዋል።

በፖሊሲው ላይ አሳታፊ እና ግልጽ ውይይት መደረጉን አስታውሰው የፖሊሲው ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ የተመላከቱትን ማስተግበሪያ ስልቶች የሚተገብሩ ተቋማትን ለማቋቋም የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች በመዘጋጀት ላይ ናቸው ብለዋል።

የጃፓን መንግስት በሕግ ረቂቆቹ ላይ የሚደረጉት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ጨምሮ በፖሊሲ ትግበራ ፍኖተ ካርታው ላይ የተመላከቱትን ተግባራት በመተግበር ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ በበኩላቸው፤ ጃፓን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደምትግፍ ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ዴሞክራሲን ለማስፈን ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራቸው የትግበራ ሂደቱን ለመደገፍ ዝግጁ ናት ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ጃፓን በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ማዕቀፍ ለማዘጋጀት መስማማታቸው ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review