ገቢን የማሳደግ ትልምና የቤት ስራዎቹ 

ታክስ ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት ነው። መንግስታት ለህዝቡ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና መሰረተ ልማቶችን ለማቅረብ ከታክስ እና ልዩ ልዩ ምንጮች ገቢ ይሰበስባሉ። አዲስ አበባ ከተማም ከታክስና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የምትሰበስበው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ 15 ቢሊዮን ብር ወይም 23 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ የባለፉት ሁለት ዓመታት ተነጥሎ ሲታይ የ33 በመቶ አማካይ እድገት እንዳለው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

በ2010 ዓ.ም 33 ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር የነበረው ገቢ የመሰብሰብ አቅም በ2011 በጀት ዓመት ወደ 39 ነጥብ 19 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የተሰበሰበው  ገቢ 146 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ ሰብአዊ ልማትና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከታክስና ከተለያዩ ምንጮች ገቢ ይሰበስባል፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም 230 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል፡፡

ይህን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት እና የታክስ መሰረቱን ለማስፋት ምን ዓይነት ስራዎች እየተሰሩ ነው? ምንስ መሰራት ይኖርበታል? ስንል የአዲስ አበባ ገቢዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች፣ የከተማው የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን በማነጋገር እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት 3 ሺህ 961 የደረጃ “ሀ”፣ 2 ሺህ 920 የደረጃ  “ለ”፣ 17 ሺህ 477 የደረጃ ሐ በድምሩ 24 ሺህ 358 ግብር ከፋዮች ይገኛሉ፡፡

በክፍለ ከተማው በ2016 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 43 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ነጥብ 51 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 103 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ የኋላወርቅ ለማ ይገልጻሉ፡፡

“ሁሉም ታክስ ከፋዮች ግብራቸውን የሚያሳውቁ ከሆነ የታቀደውን ገቢ መሰብሰብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ግብር ከፋዮች እንዲከፍሉ በማስታወቂያ ወይም በሌላ መንገድ ስለተነገረ ብቻ አይመጡም፡፡” የሚሉት ወይዘሮ የኋላወርቅ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እያንዳንዱን ግብር ከፋይ በቅርበት መከታተል እንደሚያስፈልግና ለዚህም ሁሉም አመራርና ሰራተኛ ኃላፊነት በመስጠት እንደሚሰራ ነግረውናል፡፡

ወደ ገቢ ስርዓቱ ያልገቡትን ለማስገባት ጠንካራ ክትትል ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ከቤት ኪራይ ገቢ እያገኙ የቤት ኪራይ ግብር፣ ደመወዝ እያገኙ የስራ ግብር የማይከፍሉ፣ ገቢያቸውን አሳንሰው የሚያሳውቁ፣ አዳዲስ የተገነቡ ህንፃዎችን አከራይተው ወደ ግብር ስርዓቱ ያልገቡትን ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ ጭምር በመፈተሽ እንዲገቡ ማድረግ ከተቻለ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ማሳካት ይቻላል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ከሰራተኛውና በየደረጃው ከሚገኝ አመራር ጋር መግባባት በመፍጠር እንደሚሰራ አንስተዋል፡፡

ሌላው ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን እንዲከፍል ውሳኔን በቶሎ ማድረስ ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ውሳኔዎች በቶሎ የማይደርሱ ከሆነ ግብር የሚሰበሰብበት ጊዜ ይራዘማል ያሉት ወይዘሮ የኋላወርቅ፣ ከዚህ አንጻር ውሳኔን በተገቢው ጊዜ ለማድረስ ይሰራል፡፡

ሌላኛው ክፍተት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አጠቃቀም ወይም ደረሰኝ መቁረጥ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የክትትልና ቁጥጥር ስራው በዋናነት በመደበኛ የስራ ሰዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ ከመደበኛ የስራ ሰዓት ውጪ ለምሳሌ ቅዳሜ ከሰዓት እና እሁድ የሚካሄዱ በርካታ ግብይቶች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር የማይደረግ መሆኑ በደረሰኝ አጠቃቀም ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ነው፡፡ እነዚህን ግብይቶች ለመከታተል ተጨማሪ የሰው ሀይል፣ ፖሊስና ሌሎች ግብአቶች ማሰማራት እንደሚጠይቅ ያነሳሉ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ በ2016 በጀት ዓመትም 17 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 103 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ የነገሩን ደግሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ ኃ/ሚካኤል ናቸው፡፡

ዕቅድን ማሳካት የተቻለበት ምክንያትም በዓመቱ መጀመሪያ ከአመራሩ፣ ሰራተኛውና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ግንዛቤና መግባባት በመፍጠር ስራ በመገባቱ እንደሆነ ወይዘሮ ሙሉ ይገልፃሉ፡፡ የቦታና የቤት ኪራይ ግብር ላይ ማሻሻያ መደረጉ፣ በ2015 ዓ.ም መሰብሰብ የነበረባቸው ውዝፍ ክፍያዎች በተለይ የህንፃ ኪራይ ግብር ገቢዎች መሰብሰባቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ተቋማት ግዥዎችን ሲፈፅሙ ይዘው የሚያስቀሩትን ክፍያ የመሰብሰብ ኃላፊነትም የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊነት ተሰጥቶት ስለነበር የተሰበሰበው ገቢ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ተቋማት ግዥዎችን ሲፈፅሙ የሚከፍሉትን ክፍያ የመሰብሰብ ኃላፊነት ወደ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ እንዲሄድ መወሰኑን ወ/ሮ ሙሉ ጠቁመዋል። በ2016 በጀት ዓመት የአራዳ ገቢዎች ቅርንጫፍ በራሱ አቅም 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 2 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 97 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል፡፡

ይህም ባለፈው ዓመት በራስ አቅም ከተሰበሰበው የአንድ ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያለው ሲሆን፣ ይህን ከፍ ያለ ዕቅድ በተለመደው መልኩ በመሄድ ማሳካት የማይቻል በመሆኑ ያሉ አማራጮችን በደንብ ማየትና ከሚመለከታቸው አመራሮችና ሰራተኞች ጋር መግባባት በመፍጠር መስራት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ንግድ ስርዓቱ ገብተው ወደ ታክስ መረቡ በመግባት የሚጠበቅባቸውን የማይከፍሉትን እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል፡፡

የታክስ ህግ እንዲከበር በተለይ የደረጃ ሀ እና የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች ላይ የሚታየውን በደረሰኝ ያለመገበያየት ችግርን ለመቅረፍ የሒሳብ መመዝገቢያ ማሽንና የእጅ በእጅ ደረሰኝ እንዲጠቀሙ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚጠናከር ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ምን ይላል?

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ እንደ ከተማ በ2017 በጀት ዓመት ከሚሰበሰበው ከ230 ነጥብ 39 ቢሊዮን ብር የገቢ ዕቅድ ውስጥ 156 ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚሆነው በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ይሰበሰባል፡፡ ቀሪውን የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የመሬት ይዞታና መረጃ ምዝገባ ኤጀንሲ፣  የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ንግድ ቢሮ ያሉ 32 የሚደርሱ የከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና 11 ክፍለ ከተሞች ድርሻቸውን  ይወስዳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ

የተያዘውን የገቢ እቅድ ለማሳካት ሰፊ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ የቢሮው ኃላፊ አቶ አደም ያብራራሉ፡፡ የታክስ መሰረት የሚሰፋው በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛ አዳዲስ የታክስ አርዕስቶች ሲተገበሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው በፀደቁ የታክስ ገቢ አርስቶች ወደ ግብር ስርዓቱ ያልገቡ እንዲገቡ ሲደረግ ነው። የታክስ ክፍያ ምጣኔውን ማሻሻልም ሌላኛው መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም አማራጮች በአዲስ አበባ ከተማ የፋይናንስ ቢሮ፣ የገቢዎች ቢሮ ወይም የከተማ አስተዳደሩ ስልጣን የሚወሰኑ አይደሉም፡፡ የፌዴራል መንግስት ወይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉ አቶ አደም ያነሳሉ።

የታክስ ገቢ ምጣኔን ብናነሳ ለምሳሌ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) የማስከፈያ ምጣኔ 15 በመቶ ነው፡፡ ይህንን ምጣኔ መቀየር ቢያስፈልግ ኃላፊነቱ የፌዴራል መንግስት ነው። እንደ የአዲስ አበባ ገቢዎች በተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ወይም መግባት ኖሮባቸው ያልገቡትን በመፈተሽ ወደ ግብር ስርዓቱ እንዲገቡ በሰፊው ይሰራል፡፡

የማዘጋጃ ቤታዊ ታክስና የአገልግሎት ክፍያዎችን የከተማ አስተዳደሩ እያጠና የሚተገብራቸው ናቸው፡፡ በመርህ ደረጃ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲያቀርብ የሚከፈለው ክፍያ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ ካልሆኑ በስተቀር ቢያንስ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚወጣውን ወጪ የሚመልሱ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ አንድ የንግድ  ወይም የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚያወጣ ሰው ቢያንስ ያንን አገልግሎት ለመስጠት የወጣውን ወጪ የሚተካ የአገልግሎት ክፍያ መፈፀም ይኖርበታል። ይህንን የማሻሻል ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ እንደመሆኑ እየፈተሸ የማስተካከል እርምጃ ይወስዳል፡፡ በፋይናንስ ቢሮ አስተባባሪነት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ጥያቄ አቅራቢነት የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያዎች ይደየከተማ አስተዳደሩ የታክስ መሰረቱን ለማስፋትና ለማሳደግ በተፈቀዱትና አሁን ስራ ላይ ባሉት የገቢ መሰረቶች ላይ ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡ ግብር ከፋዮች እንዲገቡ ይሰራል፡፡ ወደ ንግድ ስርዓቱ ገብተው ግብር የማይከፍሉ፣ ደመወዝ እያገኙ አሰሪዎቻቸው የደመወዝ ግብር የማይሰበስቡ፣ ቤት እያከራዩ ከሚያገኙት ጥቅም ታክስ የማይከፍሉ እንዳሉ ያነሱት አቶ አደም፣ እነዚህን ወደ ታክስ ስርዓቱ በማስገባትና የሚጠበቅባቸውን እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡

ለምሳሌ የቤት ኪራይ ገቢ ታክስ ተግባራዊ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከተማዋ ላይ ያሉ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ግብር ስርዓቱ አልገቡም። የቤት ኪራይ ግብር ህጉ ከወጣ ከ45 ዓመት በላይ ሆኖታል። ነገር ግን ድሮ በነበረው ምጣኔ የሚሰበሰበው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ያለ የቤት ኪራይ ግብር ተመን ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ወደ ስርዓቱ ያልገቡ ተከታትሎ እንዲከፍሉ በማድረግ የታክስ መሰረቱን ከፍ እንዲል ይደረጋል።

ሌላው የታክስ መሰረቱን ማስፋት ሲባል ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡትን ብቻ ሳይሆን ወደ ስርዓቱ ገብተው አነስተኛ ታክስ የሚከፍሉትም ባገኙት ጥቅም ልክ እንዲከፍሉ መስራትን ይጠይቃል። ለምሳሌ በደረሰኝ መገበያየት ሲጠበቅባቸው ያለደረሰኝ በመገበያየት ገቢን የሚደብቁትን ፈልጎ ማስከፈል፣ የቤት ኪራይ ገቢ ግብር የሚከፍሉ ሆነው ነገር ግን ልኬታቸውን በማሳነስ የሚከፍሉትን እንደገና ልኬት እንዲከናወን በማድረግ ምጣኔን ለማስጠበቅ ይሰራል፡፡

ከክትትልና ቁጥጥር ባሻገር ህብረተሰቡ ታክስ የሚከፈለው ለከተማና ለሀገር ልማት መሆኑን፣ የዜግነት ግዴታው መሆኑን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ በገጽ ለገፅ፣ በሬዲዮና ቴሌቭዥን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ትምህርት ይሰጣል። የተሰበሰበው ገቢ ለምን እየዋለ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮና የከንቲባ ፅህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት የተሰሩ ልማቶችን በማስተዋወቅና በማስጎብኘት ግልጽነት ለመፍጠር ይሰራል፡፡

እንደ ሆቴል፣ መጠጥ ቤቶች ያሉ በምሽት የሚከናወኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች የደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘም ክትትልና ቁጥጥር ከማድረግ አንጻር በልዩ ሁኔታና በተጠና መንገድ እንደሚከናወን አንስተዋል። የኮሪደር ልማቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ጭምር እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሌሊት ግብይቶች እየሰፉ ሲመጡ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ቁመናውን በዚያው ልክ እያጠናከረ ይሄዳል፡፡ አሁን ላይ ግን አብዛኛውን ክትትልና ቁጥጥር የሚደረገው ቀን ላይ በሚካሄዱ ግብይቶች ነው፡፡ በስራ ባህርያቸው በምሽት ላይ ሰፊ ግብይት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በልዩ ሁኔታና በተጠና መልኩ የሚካሄደው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡ 

በቅርቡ በተካሄደው በ“ግብር ለሀገር ክብር” ንቅናቄ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ በ2017 በጀት ዓመት ሊሰበሰብ የተያዘው ዕቅድ ከፍ ያለ ቢሆንም ከከተማዋ ገቢ የማመንጨት አቅም አኳያ ሲታይ በጣም ትልቅ የሚባል አይደለም፡፡ እቅዱ የተለየ ግብር በመጨመር ሳይሆን ሳይሰበሰብ የሚቀረውን በመሰብሰብ የሚሳካ እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡ “የግብር ስወራ በትክክል ከተዋጋን ከዚህ በላይ መሰብሰብ እንደምንችል ያለው ጥናት ያሳያል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን” ብለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ምሁራን ምን ይላሉ?

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንዳብራሩት አዲስ አበባ በ2017 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የያዘችው የገቢ ዕቅድ ትልቅ ትርጉም ያለውና የከተማዋን እድገት ለማስቀጠል የሚያግዝ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

ይህንን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ከታክስና ከተለያዩ ምንጮች ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ተሽከርካሪዎች ለግማሽ ሰዓት መንገድ ላይ ሲቆሙ ላገኙት አገልግሎት (ፓርኪንግ) እንደሁኔታው ከአራት እስከ ስድስት ብር ይከፍላሉ፡፡ ከፓርኪንግ የሚሰበሰበው ገንዘብ በተደራጀ መንገድ ቢሰራበት ለከተማዋ ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት ያስችላል፡፡ አምራች ድርጅቶችም በደንብ ተንቀሳቅሰው ህጋዊ ሆነው የሚሰሩ ከሆነ የተያዘውን ገቢ መሰብሰብ አያስቸግርም ይላሉ፡፡

ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጭ የሚሰበሰብ ገቢ አስተማማኝ እንደሆነ የሚናገሩት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ዘካሪያስ ሚኖታ በበኩላቸው ከተማዋ የምትሰበስበውን የገቢ አቅም ለማሳደግ በዋናነት ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ስራ በመስራት ገቢያቸውን የሚያሳድጉበትን መንገድ ላይ መስራት እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡

ሰዎች ወደ ስራ የሚገቡ ከሆነ ሀብት ያፈራሉ፡፡ ሀብት ሲያፈሩ ደግሞ የተወሰነም ቢሆንም ስለሚቆጥቡ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ገንዘብ ይኖራል፡፡ ይህም እንደገና ስራና ሀብት በመፍጠር የሚሰበሰበው ገቢ እንዲያድግ ዕድል ይፈጥራል። በዚህ ረገድም ግልጽ ፖሊሲዎችንና አሰራሮችን በማውጣት ለሚሰሩ ሰዎች ብድር በማመቻቸት፣ የንግድ ፈቃድና አስተዳደር፣ የግብር አስተዳደሩን ቀላል በማድረግ፣ ሰፋፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚቻል ከሆነ የዜጎች ወይም የንግድ ማህበረሰቡ ገቢ ይጨምራል፡፡ የገቢ መጨመር ደግሞ ዞሮ ዞሮ የሚሰበሰበው ግብር እንዲያደግ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘም ሁሉም በንግድ ስራ የተሰማሩ ወይም ግብር መክፈል ያለባቸው ሁሉ እንዲከፍሉ ማድረግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ዘካሪያስ ያስገነዝባሉ፡፡ አንዱ እየከፈለ ሌላው የማይከፍል ከሆነ ኢ-ፍትሀዊነትን ያመጣል። ታክስ መደበቅና ስወራንም ያበረታታል፡፡ ከዚህ አኳያ ግብር መክፈል ያለበት አካል የትኛው እንደሆነ መረጃዎችን በትክክል በመያዝ መክፈል ያለባቸው እንዲከፍሉ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ፋሲል ጣሰው አዲስ አበባ ትልቅ፣ በርካታ አምራች ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙባትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ከተማ በመሆኗ ሰፊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም አላት። በዚህ ረገድ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ማዘመን እንደሚገባ ያነሳሉ። ለምሳሌ የፋይናንስ ተቋማት ዕለታዊ የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ እንደመሆኑ ዕለታዊ የታክስ ምጣኔ መጣል ያሉ አማራጮችን ማየት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከሳምንታት በፊት “ግብር ለሀገር ክብር” የንቅናቄ መድረክ ላይ እንደገለፁት፣ ከግብር ከፋዮች የሚጠበቀውን ገቢ መሰብሰብ መቻሉ የነዋሪዎችን ችግር ያቃለሉ የተለያዩ ልማቶችን ለማከናወን አስችሏል፡፡ በ2016 በጀት ዓመት የኮሪደር ልማትን ሳይጨምር 18 ሺህ 91 ፕሮጀክቶችን መፈጸም ተችሏል፡፡ ይህም የተሰበሰበው ግብር ስራ  ላይ እየዋለ መሆኑን አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን ለኑሮ የምትመች ከተማ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ሰፋፊ ትልሞችን በመያዝ እየተገበረ ይገኛል፡፡ በየዓመቱም የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚሰበሰበው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ ሲሆን የተያዘውን የገቢ ግብር ዕቅድ ለማሳካት ያሉ አቅሞችን ሁሉ አሟጥጦ መጠቀም ይገባል እንላለን፡፡

ስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review