ገና በኢትዮጵያ እና በሌሎች የዓለም ሀገራት

You are currently viewing ገና በኢትዮጵያ እና በሌሎች የዓለም ሀገራት

AMN – ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም

የጎርጎሮሳዊያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ የዓለም ሀገራት ገናን አክብረው፣ አዲስ ዓመት ተቀብለው፣ የገና ዛፍ ከቤታቸው አውጥተው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ሲጀምሩ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሩሲያ፣ ግብጽ፣ ቤላሩስ፣ ጆርጂያ፣ መቄዶኒያ፣ ካዛኪስታን፣ ሞልዶቫ፣ ሞንቴኔግሮ እና ሰርቢያ ደግሞ የገና በዓልን ታህሳስ 29 በዛሬው ቀን ያከብራሉ፡፡

እነዚህ ሀገራት የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ መሆናቸው ነው ከጎርጎሮሳዊያኑ የገና በዓል 13 ቀናት በኋላ ገናን እንዲያከብሩ ያስቻላቸው፡፡

ኢትዮጵያም ከክርስቶስ ልደት ጋር የተያያዘ የዘመን አቆጣጣር የምትከተል ሀገር እንደመሆኗ በዛሬው እለትም መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የክርስቶስን ልደት በማሰብ በዓሉን በድምቀት እያከበሩት ይገኛል፡፡

የገና ጨዋታ በዓሉ በኢትዮጰያ ከሀይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ባህላዊ መልክ እንዳለውም አመላካች ነው፡፡

በግብጽ የሚገኙ 15 ሚሊዮን የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተከታዮችም የገና በዓልን በዛሬው ዕለት እያከበሩ ነው፡፡ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተከታዮች በሀገሪቱ 90 በመቶ የሚሆነውን የክርስትና እምነት ተከታዮችን ቁጥር ይሸፍናሉ፡፡

በሩሲያም የገና በዓል ዋዜማን በጾም የሚያሳልፉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዛሬው እለት የገና በዓልን በማክበር ላይ ይገኛሉ። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም እንደተለመደው በክሬምሊን በሚገኘው ካቴድራል የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመዋል፡፡

በመቄዶኒያ ከገና በዓል ቀደም ብሎ ባለው ቀን ሌሊቱን እሳት ተቀጣጥሎ በመኖሪያ ግቢም ሆነ በአደባባይ ላይ እስኪነጋ ድረስ ይበራል፡፡ ይህ ሥርዓትም ባንዲክ ይሰኛል፡፡

ህጻናት በማለዳ ተነስተው በቡድን ሆነው በየቤቱ በመዞር እያዜሙ የበዓሉን ድባብ ያደምቁታል፡፡ በዚሁ ወቅት ህጻናቱ ከጎረቤቶቻቸው ሥጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡

ሞንቴኔግሮም ከመቄዶኒያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የገና በዓል አከበባር የምትከተል ሀገር ናት፡፡

በሌሎች ሀገራት የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉን በተለያዩ ሀይማኖታዊ ሥርዓቶች፣ ባህላዊ ክዋኔዎች፣እንደየሀገራቱ ባህል የተወደዱ ምግቦችን በማዘጋጀት፣ ቤት በማሳመር፣ ወዳጅ ዘመድ በመጠየቅ፣ ሥጦታ በመለዋወጥ፣ አቅመ ደካሞችንን በማገዝና በመመገብ እለቱን አክብረው እንደሚሳያልፉ ከተለያዩ ድረ ገጾች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review