ጉግል ኩባንያ የካናዳ የዜና ይዘቶችን ለመጠቀም 100 ሚሊዮን ዶላር ከፈለ

You are currently viewing ጉግል ኩባንያ የካናዳ የዜና ይዘቶችን ለመጠቀም 100 ሚሊዮን ዶላር ከፈለ

AMN – ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም

የጉግል ኩባንያ የካናዳ ዜና ይዘቶችን ለመጠቀም 100 ሚሊዮን ዶላር ለዜና ድርጅቶችና አሳታሚዎች መክፈሉን የቴክኖሎጂ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ኩባንያው ስምምነት ላይ የደረሰው የካናዳ ምክር ቤት አወዛጋቢ የሆነውን የኦንላይን ዜና ረቂቅ ሕግን ካጸደቀ በኋላ ነው።

ረቂቅ ሕጉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በገጻቸው ላይ ለሚታተሙ ይዘቶች ለዜና አሳታሚዎች እንዲከፍሉ ያስገድዳል።

ይህንን ተከትሎም ጎግል እና ሜታ ኩባንያ ለካናዳ ጆርናሊዝም ኮሌክቲቭ (CJC) የዜና ማሰራጫዎች ይዘቶችን ለመጠቀም እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር።

በዚህም ጉግል ኩባንያ የካናዳ የዜና ይዘቶችን ለመጠቀም 100 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ ተነግሯል፡፡

በተቃራኒው ሜታ ኩባንያ ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን ጨምሮ በሚያስተዳድራቸው በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ላይ የሚቀርቡ የካናዳ ዜናዎች ላይ ገደብ ጥሏል፡፡

በጉግል ስምምነት መሠረት ከ100 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው ለቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚከፋፈል ሲሆን የቀረው ደግሞ ለዜና አሳታሚዎች የሚከፈል ነው፡፡

የሚዲያ ኢንደስትሪ ግሩፕ የሆነው የኒውስ ሚዲያ ካናዳ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፖል ዲጋን እንደገለጹት፣ ገንዘቡ እየተንገዳገዱ ያሉት የዜና ድርጅቶችን ለማጠናከር ያግዛል፡፡

ገንዘቡ የዜና ድርጅቶቹ የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ተቋማት መረጃዎች በጥራት እንዲያዘጋጁ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይም ስምምነቱ ጉግል በጋዜጠኞች የተዘጋጁ በእውነታ ላይ የተመሠረተና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ዕድል ይፈጥርለታል ማለታቸውን ሲቢሲ ኒውስ አስነብቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review