ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የሌሎችን ተጠቃሚነት የሚፃረር እና አለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው- ኢንጂነር ተፈራ በየነ

You are currently viewing ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የሌሎችን ተጠቃሚነት የሚፃረር እና አለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው- ኢንጂነር ተፈራ በየነ

AMN – ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም

ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችው አቋም የሌሎችን ተጠቃሚነት የሚፃረር እና የአለም አቀፍ ህግን የጣሰ መሆኑን በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ውሃዎች አማካሪ ኢንጂነር ተፈራ በየነ ተናገሩ።

ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኢንጂነር ተፈራ፣ ኢትዮጵያ የጋራ መልማትን አብዝታ በመሻት የናይል ወንዝ ትብብር ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ለበርካታ አመታት አበክራ ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

ለረጅም ዘመናት እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል መርህን በማንገብ ስትሞግትና የተፈጥሮ ሀብቱን ለብቻዋ ስትጠቀም የቆየችው ግብፅ ይህንን ለጋራ እንልማ ጥያቄን አለመቀበሏን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በግብፅ የሚነሱ የቅኝ ግዛት ውሎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ያነሱት ኢንጂነር ተፈራ በየነ ፣ ግብፅ የምታነሳቸው ሃሳቦች የሌሎችን ተጠቃሚነት የሚፃረር መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በርካታ የውሀ ማመንጫ ሀይል ያላቸው ሀገራት ፍታሃዊነትን በሚፃረረው ውል የተነሳ ለዘመናት ከፍተኛ ችግርን ሲያስተናግዱ መቆየታቸውን በማስታወስ ኢትዮጵያ የሄደችበት ርቀት ትምህርት ሰጪ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የአባይን ወንዝ ሰፊ ድርሻ የያዘችው ኢትዮጵያ በጋራ እንልማ ጥሪ ለቀጠናው ከፍ ሲልም ለአህጉሪቱ በርካታ ትሩፋት እንዳለውም አማካሪው ገልጸዋል።

ከጥቅምት 3/2017 ጀምሮ ወደ ተፈፃሚነት የገባው የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በቀኝ ግዛት ውሎች ፍትሃዊነት የጎደለውን መንገድ የሚሰብር ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡

የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከጥቅምት 3/2017 ጀምሮ ወደ ተፈፃሚነት መግባቱ ይታወሳል፡፡

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review