ግጭት ይብቃ ፤ ክላሽ ይውረድ፤ በሰላማዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንነጋገር ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ግጭት ይብቃ ፤ ክላሽ ይውረድ፤ በሰላማዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንነጋገር ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥር 23/2017 ዓ.ም

ግጭት ይብቃ ፤ ክላሽ ይውረድ፤ በሰላማዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንነጋገር ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡

መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር እና ለመደራደር ግማሽ መንገድ መሄድን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

2ኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልእክት የመጀመርያው ጉባዔ የመነሳት ምዕራፍ ነበር ፣ አሁን ያለንበት ሁለተኛው ምእራፍ የማንሰራራት ዘመን ነው ብለዋል፡፡

ይህም የቁልቁለት እና የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበት ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያውያን በመተባበር እና በወንድማማችነት በጋራ ራዕይ የምንሰራበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዱ ሌላውን ተጭኖ ቀምቶና ዘርፎ የሚኖርበት ዘመን ያለፈ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ያለንን ጸጋ በማወቅ እና ይበልጥ አልቆ በመስራት እንዲሁም የሰራነውን በማሻሻል በቀጣይ ለውጥ ማምጣት ይገባናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍጠር ደግሞ በተለመደው ሳይሆን ነገሮችን በአዲስ መልክ እና መንገድ በመመልከት ሊሆን እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

ነገሮችን በጭንቅላት ውስጥ ጨርሶ በተጨባጭ መጨረስ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

መፍጠር ሌላው በሁለተኛው ምእራፍ ልንተገብረው የሚገባ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ የለንም በሚል እሳቤ ልማታችንን በማፋጠን ለለውጥ መስራት እንደሚገባ አውስተዋል፡፡

በዚህም የተጀመረውን ስንዴ ወደ ውጭ የመላክ ፤ህዳሴ ግድብን መጨረስ ሌላው የምንተጋበት ስራ ነው ሲሉ አስምረውበታል፡፡

ከዚህ ጉባኤ በኋላ በሚቀጥሉት ወራት የምናስመርቃቸው ፕሮጀክቶች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻራችንንም የምናኖርባቸው ትልልቅ የልማት ስራዎች አሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አሁን የጀመርናቸውን ጨርሰን የተለያዩ ብስራቶችን የምናበስርበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

ጊዜው የማንሰራራት እና በጎ ጉዳዮችን የምናበስርበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥለው ዓመት የኮሪደር ልማቱ አልቆ እና ልቆ የሚታይበት እንደሚሆንም አረጋግጠዋል፡፡

ጉባኤው አሰራርን በመቀየር አዲስ እና የተሻለ የስራ ባህል የምናዳብርበት ፤ የተሻሉ ሀሳቦች የሚፈልቁበት እንደሚሆን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና 15 ነጥብ 7 ሚሊየን አባላት ያሉትና በአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ፓርቲው ከፍተኛ ቁጥር ያለው እና በወጣቶች የተሞላ ፓርቲ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ለልጆቻችን እዳ ሳይሆን ምንዳን ማውረስ ይኖርብናል ብለዋል፡፡ለልጆቻችን ብልጽግናን ማውረስ ይኖርብናልም ነው ያሉት፡፡

ብልጽግና ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስንም የተለማመደ ፓርቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ልጆቻችንን እያሰብን ለለውጥ እንትጋ ብለዋል፡፡

ግጭት ይብቃ ፤ እንነጋገር ፤ ክለሽ ይውረድ በሰላማዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንነጋገር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር እና ለመደራደር ግማሽ መንገድ መሄድን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአገሪቱ ዋና አጀንዳ ሰላም እና አንድነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ እንደ ትናንቱ ሁሉ ከፊታችን ፈተናዎች ቢኖሩም ፈተናዎችን ተሻግረን ብልጽግናን እናወርሳለን ብለዋል፡፡

ለጉባኤው አዘጋጆችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሰለሞን በቀለ

All reactions:

246246

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review