ጠላቶች የከፈቱብንን ጦርነቶች በመመከት ሀገርን አስከብረው ለዚህ ትውልድ ያስረከቡ የየዘመኑ ጀግኖች የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ናቸው -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

You are currently viewing ጠላቶች የከፈቱብንን ጦርነቶች በመመከት ሀገርን አስከብረው ለዚህ ትውልድ ያስረከቡ የየዘመኑ ጀግኖች የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ናቸው -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ጠላቶች የከፈቱብንን ጦርነቶች በመመከት ሀገርን አስከብረው ለዚህ ትውልድ ያስረከቡ የየዘመኑ ጀግኖች የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ናቸውና እንዘክራቸዋለን ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ በሚገኘው 116ኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ረጅም ዕድሜ ያላት ቀደምትና በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ድረስ የዘለቀች ታላቅ ሀገር መሆኗን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ ረጅም የታሪክ ዘመናትም በየትውልዱ በነበሩ ልጆቿ ተጋድሎ ነጻነቷ ተጠብቆ የተላለፈችልን ሀገር ናት ያሉት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ነገር ግን መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር እሴቶቿ እየፈራረሱ በመሄዳቸው ያለፉት ገድሎችና ጀግኖች እየተዘነጉ መጥተዋል ብለዋል፡፡

ትውልዱ የተግባባበት የጋራ ታሪክ ባለመኖሩ ምክንያት በአንድነት ቆሞ ሀገሩን ከመገንባትና ከድህነት ከማላቀቅ ይልቅ ገዢዎች በሚሰጡት አጀንዳ ጎራ ለይቶ ለመናቆር ተገዷል ነው ያሉት፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሪፎርም ሲያካሄድ ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ሰራዊቱን ከብሄርና ከፖለቲካ ወገንተኝነት በማላቀቅ በኢትዮጵያዊነት ፀንቶ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በእኩልነት የሚያገለግል እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ሰራዊቱን በስነልቦና የመገንባት ስራ አስፈላጊ በመሆኑ ሀገራዊ ተጋድሎና የአርበኝነት ታሪክን እንደ አንድ የሰራዊት ግንባታ መነሻ መጠቀም አንዱ መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አንስተዋል፡፡

ጥቅምት 15/1900 ዐጼ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስቴር መስርያ ቤትን ያቋቋሙበትና መስርያ ቤቱን የሚመሩ ሚኒስትር የሾሙበት እንዲሁም በዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በቋሚነት ተደራጅቶ እንደ ተቋም የተመሰረተበት ቀን በመሆኑ የሰራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ጠላቶች የከፈቱብንን ጦርነቶች በመመከት ሀገርን አስከብረው ለዚህ ትውልድ ያስረከቡ የየዘመኑ ጀግኖች የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአድዋ፤በማይጨው እና በካራማራ በተካሄዱ ተጋድሎዎች የተሳተፉና መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን በዚህ በዓል ክብር ሰጥተን እንዘክራቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዘመንም ሀገራችን ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚፈልጉና የህዝቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ ቢኖሩም የሀገር ሉዓላዊነት እንዳይደፈር መደረጉን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ተግባር አኩሪ ተግባር እየፈጸመ ለሚገኘው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላት ክብር ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡

“እኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት የቀደሙትን ጀግኖች አደራ በመጠበቅ ሉዓላዊነቷ ሳይደፈር የተረከብናትና ሀገር እንደታፈረች እና እንደተከበረች ለማስቀጠል ወታደራዊ ቁመናችንን አሳድገንና አዘምነን ተልዕኮዋችንን በላቀ ብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነን” ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr

Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9

Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8

Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review