ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ አስታወቀች

AMN-ኅዳር 18/2017 ዓ.ም

ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ጣሊያን የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኗን በተለይም በልማት ትብብር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ የምታደርገውን ጠንካራ ተሳትፎ ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ እና እንደምታመሠግን ገልጸዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በመሪዎች ደረጃ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ በመግለጽ ሚኒስትር ዴኤታው እየተካሄደ ያለው ጉብኝትም የሁለቱን አገራት የትብብር አድማስ ለማስፋት እና አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ጣሊያን በአፍሪካ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያወጣችው የማቴ ዕቅድ(Mattei Plan) የኢትዮጵያም የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከመጥቀሙ ባሻገር ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ አንስተዋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ በበኩላቸው በመንግሥታቸው ኢትዮጵያ ትኩረት የሚሰጣት አገር መሆኗን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዎቹ በውይይታቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የልማት ትብብር ስምምነት በአዲስ መንፈስ መቃኘት እንደሚያስፈልግ መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review