ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

You are currently viewing ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከጣሊያን የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ሚኒስትር አና ማሪያ በርኒኒ ጋር የኢትዮጵያን ዲጂታል ለውጥ እና በፈጠራ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገትን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ የጣሊያን መንግስት ኢትዮጵያ ጠንካራ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማምጣት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ለማጎልበት ለምታደርገው ጥረት የ585 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መስጠቱን አመስግነዋል።

ሚኒስትሩ ይህ አጋርነት የኢትዮጵያን ዲጂታል መሠረተ ልማት ለማዘመን፣ ልማትን ለማስፋፋት እና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሰው ሀብት አቅም ግንባታ ስራን ለመስራት የታቀዱ የተለያዩ ውጥኖችን ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂና ፈጠራ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና ቴክኖሎጂን ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት በማዋል ረገድ ምቹ ስነምህዳርን ለመፍጠር የትብብሩ አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

አና ማሪያ በርኒኒ በበኩላቸው፤ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀው፤ የዲጂታል ፈጠራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ያለውን የለውጥ አቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ በኒዩክለር ሳይንስ እና በምርምር ዘርፍ ጣሊያን በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመ የትምህርት ልውውጥ መርሃ ግብሮችን እና የጋራ የምርምር ስራዎችን ጨምሮ የወደፊት የትብብር መስኮች ላይም መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review