ጣና ነሽ ጀልባ ከጂቡቲ ዶራሌ ፈርጀ-ብዙ ወደብ አገር ቤት ዛሬ ጠዋት ጉዞ ጀምራለች።
የጣና ነሽ ጀልባ 150 ሜትሪክ ቶን ክብደት የምትመዝን፣ 38 ሜትር ርዝመት ያላት እና 200 ተሳፋሪ የመያዝ አቅም ያላት ሲሆን ለመዝናኛ አገልግሎት በመጠቀም በሀገራችን እያደገ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትልቅ አስተዋጾ የምታበረክት ይሆናል ።
ጀልባዋ ከጅቡቲ ተነስታ በዲኪል-ካላፊ መንገድ የምትንቀሳቀስ ሲሆን፣ በአማካይ በ7 ቀናት በኃላ ኮሪደሩን ታቋርጣለች ተብሎ ይጠበቃል። ለጉዞ የሚሆን የዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የሃይል ተሸካሚ መስመሮች በኮሪደሩ የሚቋረጡና ተለዋጭ መንገድ የተዘጋጀላቸው ሲሆን፣ ሁለት ተጨማሪ ጎታች ተሽከርካሪዎች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች ተመድቦ ከጀልባዋ ጋር ጉዞ ጀምሯል።
የጣና ነሽ ጀልባ ላለፉት ጊዜያት አስፈላጊው ክትትል ሲደረግላት የቆየ ሲሆን፣ በአማካኝ ከ3 ወራት በኃላ ጎርጎራ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ጅቡቲ ከሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።