ጥቂት ስለ ጆሀንስበርግ ከተማ

You are currently viewing ጥቂት ስለ ጆሀንስበርግ ከተማ

የአዲስ አበባ እህት ከተማ የሆነችው ጆሀንስበርግ ቱጃሯ የደቡብ አፍሪካ ከተማ ናት።

ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ጆሀንስበርግ ከዓለማችን 100 ትላልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።

ከተማዋ የጋውተንግ ግዛት ዋና ከተማም ጭምር ስተሆን ግዛቲቱ በደቡብ አፍካ ከሚገኙ ግዛቶች መካከል እጅግ ሀብታም እንደሆነች ይገለጻል።

የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ማዕከል የሆነችው ከተማዋ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 16 በመቶ ያህል ታበረክታለች። ከጋውተንግ ግዛት አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ደግሞ 40 በመቶ ድርሻ አላት።

የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የሀገሪቱ ትላልቅ ድርጅቶች እና ባንኮች ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫም ናት።

በወርቅ ክምችቱ የሚታወቀው ዊትስትራንድ የተሰኘው ሥፍራ ከተማዋን ዓለም አቀፍ የማዕድን እና የወርቅ ንግድ ማዕከል አድርጓታል።

በፈረንጆቹ 2008 በተካሄደው ጥናት በዓለማችን ከሚገኙ 50 የንግድ ከተሞች መካከል 47ኛ ደረጃን በመያዝ በአፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ የንግድ ማዕከል ለመሆን በቅታለች።

ዊትስትራንድ የተሰኘው ሥፍራ የወርቅ ማዕከል በፈረንጆቹ 1886 ለጆሀንስበርግ ከተማ መመሥረት ምክንያት ሆኗል። ከአሥር ዓመት በኋላም የከተማዋ ሕዝብ ቁጥር ከ100 ሺህ ማለፍ ችሏል።

የኢኮኖሚዋ መሠረት የወርቅ ሀብት ነው። ይሁንና አሁን ላይ የማዕድን ሀብት እየተመናመነ በመምጣቱ ምክንያት ኢኮኖሚው በአብዛኛው በማኑፋክቹርንግ ኢንዱስትሪው ነው ተይዞ የሚገኘው።

መንግሥት ሜትሮባስ ለተሰኘ የተቀናጀ ፈጣን የትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ በጀት መድቦ ይሠራል።

በ84 የስምሪት አቅጣጫዎችም ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በዓመት ያመላልሳል። ሜትሮ-ሬይል የተሰኘው የባቡር መሠረተልማቷ ደግሞ መካከለኛውን ጆሀንስበርግ ከሶዌቶ፣ ፕሪቶሪያ እና በዊትዎተርስትራንድ አቅራቢያ ያሉ ከተሞችን በማስተሳሰር ይታወቃል። በርግጥ የባቡር መሠረተ ልማቱ እጅግ የቆዬ መሆኑ ይነገራል።

ከፈረንጆቹ 2010 ወዲህ ፈጣን የባቡር መሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችም በከተማዋ እየተከናወነ ይገኛል።

በዓመት 28 ሚሊየን ሕዝብ በሀገር ውስጥ እና ወደ ውጭ ሀገር የሚያመላልሰው ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃን ይዞ የሚገኘው ታምቡ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፍያም እዚሁ ከተማ ነው ያለው።

በከተማዋ የሚገኘው ደረቅ ወደብ በአፍሪካ ግዙፉ ነው።

ቮዳኮም፣ ኤም.ቲ.ኤን፣ ሴል ሲ እና ቴልኮም ሞባይል የተባሉ አፕሬተሮች የቴሌኮም አገልግሎት ይሰጣሉ። የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ጨምሮ ሌሎችም የሬዲዮ እና ዲጂታል መገናኛ ብዙኃን መቀመጫ ሆና ታገለግላለች።

ጆሀንስበርግ 9 ሺህ 247 ኪ.ሜ የመንገድ መሠረተ ልማት፣ 180 ሺህ መንገድ ዳር መብራቶች፣ 1 ሺህ 780 ትራፊክ መብራቶች፣ በ84 መረሻዎች አገልግሎት የሚሰጡ 554 ዘመናዊ ባሶች፣ 9 ሺህ ኪ.ሜ ፍሳሽ ማጋጃ ቦይ፣ 600 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት የኃይል አስተላላፊ ስቴሽኖች የሚገኙባት በአፍሪካ በፈጣን ዕድገት ላይ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናት።

98 የሕዝብ መዝናኛ እና 394 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችም ለምተው ያሉባት መሆኑ ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ አድርጓል።

በተለይም ሶዌቶ (Soweto) በመባል የሚታወቀው የደቡብ ምዕራብ የከተማዋ ክፍል በሌሎች አካባቢዎች መግባት ያልተፈቀደላቸው እና በማዕድን ኢንዱስትሪው ውስጥ በጉልበት ሠራተኛነት በሚሠሩ ጥቁር አፍሪካዊያን የተመመረተች መሆኗ ይገጸላል። ይህ የከተማዋ ክፍል ከ1970 እስከ 1994 ድረስ የጆሀንስበርግ አካል አልነበረችም።

ሌናሺያ የተሰኘው ሌላኛውው የከተማዋ ክፍል ደግሞ የዘር ሐረጋቸው ከደቡብ ኢስያ የሚመዘዝ እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑ ሕንዶች የሚኖሩበት እና በቀደመው የአፓርታይድ ሥርዓት ነጮች የማይገቡበት አካባቢ ነበር።

የጆሀንስበርግ ከተማ በ2010 የተካሄደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን በድምቀት ማስተናገድ የቻለች አፍሪካዊት ከተማ ናት።

ጆሀንስበርግ አዲስ አበባን ጨምሮ ከቤጂንግ፣ በርሚንግሀም፣ ካናዳ፣ ኒውዮርክ፣ ራማላህ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ሻንጋይ እና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር በትብብር ትሠራለች፤ ተሞክሮዎችንም ትለዋወጣለች።

ብዝኃ ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋ እና ታሪክ መገኛ ስትሆን አፓርታይድ ሙዚየምን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሙዚየሞ እንዳሏት ይገለጻል።

ከሕዘቦቿ መካከል 53 በመቶው የክርስትና እምነት፣ 3 በመቶ የእስልምና፣ 1 በመቶ አይሑድ እና 1 በመቶ የሒንዱ እምነት ተከታዮጭ ናቸው። ቀሪዎቹ 14 በመቶ አፍሪካን መሠረት ያደረጉ እምነቶችን ሲከተሉ 24 በመቶዎቹ ደግሞ ለየትኛውም እምነት ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ናቸው።

በማሬ ቃጦ

AMN – ኅዳር 30/2017 ዓ.ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review