ጥቅምትን በጥበብ

የወቅቶች መፈራረቅ በሰዎች ስሜትና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ለአብነትም ኢትዮጵያ ውስጥ ሐምሌና ነሐሴ የክረምት ወቅት ነው፡፡ ክረምቱ ይዞት የመጣው ቅዝቃዜ ደግሞ ለብዙዎች ያለፈውን ትዝታ ይቀሰቅስባቸዋል፡፡ በክረምቱ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ስለሚገደብ የሚወዱትን በመናፈቅ ያንጎራጉራሉ፡፡ መስከረምና ጥቅምት ደግሞ ዝናቡና ቅዝቃዜው ረገብ ብሎ በብርሃናማ ጊዜ ይተካል፡፡ አበቦች አብበው፤ ምድር በአረንጓዴ ቅጠሎች አጊጣ፣ ሰማይ ሃምራዊ ልብስ ለብሶ፣ የክረምቱን መምጣት ተከትሎ የሸሹት አዕዋፋት ዳግም ብቅ ብለው ሲያዜሙ መመልከት መንፈስን የሚያስደስት ስሜት አለው፡፡ ታዲያ በዚህ ስሜት ነው ብዙ የሃገራችን ከያኒያን ተነሽጠው ቅኔን የተቀኙት፤ በውብ ዜማ ያንጎራጎሩት፡፡

 በሃገራችን ሙዚቃዎች፣ የግጥም ሥራዎች፣ ሥነ ቃሎች… የወራትን ባህርይ መነሻ ተደርገው የተከየኑ በርካታ የፈጠራ ሥራዎች አሉ፡፡ ለአብነትም ጥላሁን ገሰሰ፣ አስቴር አወቀ፣ ንዋይ ደበበ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አበበ ተካ… በሙዚቃ፤ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ከበደ ሚካኤል… በግጥም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከያኒያኑ ናፍቆታቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ትዝታቸውን፣ ፍቅራቸውንና ውበትን ወቅቶችን ወይም ወራትን መነሻ በማድረግ ከይነዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍም “አሁን የያዝነው ወርሃ ጥቅምት በኪነ ጥበብ ውስጥ ምን አይነት ገጽታ አለው?” በሚል አጭር ዳሰሳ አድርገናል፡፡    

በአበቦች የምትፈካው ወርሃ- ጥቅምት

ጋዜጠኛና የኪነ ጥበብ ሃያሲው ዋለልኝ አየለ “ጥቅምትና ኪነ ጥበብ ምን አይነት መስተጋብር አላቸው?” በሚል ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ “በጥቅምት ወር አበቦች ሙሉ በሙሉ የሚያብቡበት፣ ቡቃያው ወደ እሸት የሚቀየርበት ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች ልዩ መዓዛ እና ውበት የሚላበሱበት ጊዜም ነው። የኪነ ጥበብ ባለሙያው ደግሞ ጭጋጋማው የክረምት ጊዜ አልፎ ውበትና ብርሃን የተላበሱ ወራት መምጣታቸው ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርበታል፡፡ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራትም ቀላል የማይባል ጉጉት ያድርበታል፡፡ መስከረምና ጥቅምትን የሚያወሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በርከት ያሉበት ዋነኛ ምክንያትም የክረምቱ ጊዜ አልፎ በራ ወደሆኑ ወቅቶች መሸጋገራችን ነው በማለት የተለያዩ አስረጅዎችን በማቅረብ ተናግሯል፡፡ 

የጥቅምት ወር ከጥበብ ጋር ከሚያቆራኘው መካከል አበባ አንዱ ነው

በሀገራችን ለፍቅር፣ ለሃገር፣ ለቤተሰብና ለናፍቆት በርካታ ሙዚቃዎች ተሰርተዋል፡፡ ስለጥቅምት ወር እና ስለጥቅምት አበባ ከተሰሩ ሙዚቃዎች ውስጥ ደግሞ የስመጥሩ ሙዚቀኛ ንዋይ ደበበ “የጥቅምት አበባ” የተሰኘው ዘመን አይሽሬ ዘፈን በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

“የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤

የጥቅምት አበባ ነሽ አሉ፤

አወድሽው አካሌን በሙሉ።

የጥቅምት አበባ፤ የጥቅምት አበባ፤

የጥቅምት አበባ ለሽታ

ለኔ ግን ጣልሽብኝ ትዝታ…” እያለ የጥቅምት አበባ ማዐዛው የማይረሳ እና ሁልጊዜም የሚታወስ፣ የፍቅር ትዝታም እንደዛው መሆኑን ያቀነቅናል፡፡ በነገራችን ላይ በጥቅምት በተለይ በወይና ደጋ እና ደጋማ አካባቢዎች በርካታ አበቦች የሚፈኩበት ጊዜ በመሆኑ ማር የሚቆረጥበት፣ ማሩም ከተለያዩ አበባዎች የሚቀሰም ስለሚሆን ለጤንነት ሁነኛ ነው ተብሎ የሚታመንበት ጊዜም ጭምር ነው።

ድምጻዊ ንዋይ የናፈቃት ልጃገረድ እንደ ጥቅምት አበባ፣ መላ አካልን የምታውድ፣መንፈስን የምታዳርስ ከመሆኗ የተነሳ እንደ ቢራቢሮ እና እንደ ንብ ክንፍ አውጥተው ቢበሩ የማታስቆጭ መሆኗን በዘፈኑ አንስቷል፡፡ ከፍቅሩ ጋር ጠጋ ብሎ ለመወያየት ማረፊያ መፈለጉንም አይሸሽግም፡፡

“ማረፊያ አለ ወይ ፍቅርዬ 

እንዳዋይሽ ሚስጥር ጠጋ ብዬ

የጥቅምት አበባ ነሽ

አካል ሰው ነይ ናፈኩሽ

ውበት መአዛሽ ለሽታ

ፍኪልኝ ልቤ ያግኝ ደስታ…” በማለትም ጥቅምትና አበባን እንዲሁም ፍቅርን በማዋሃድ በጥቅምት ወር ብቻም ሳይሆን በየትኛውም ወር እና ዘመን ተደማጭና ተወዳጅ ሙዚቃን አበርክቷል፡፡

ድምጻዊው ፍቅርና የጥቅምት አበባን፣ አንዱ ተወድዶ አንዱን መጥላት እንደማይቻል፣ ተፈጥሮም በሃሴት፣ ተፈቃሪዋ ልጃገረድም በውበት የተሞላች መሆኗን በዘፈኑ አንጸባርቋል፡፡

ጋዜጠኛና ሃያሲ ዋለልኝ፣ ከላይ የጠቀስነው የንዋይ ደበበ ሙዚቃ የጥቅምት መዝሙር ነው ይላል፡፡ ወርሃ- ጥቅምትን በሚገባ የሚገልጽና ኪነ ጥበባዊ ልህቀቱ ላይም አንዳች እንከን የማይወጣለት ሙዚቃ ነው፡፡ መስከረምን ስናስታውስ፣ የቴዎድሮስ ታደሰን መስከረም ሲጠባ፣ የጥላሁን ገሰሰን የ13 ወር ጸጋ፣… ሐምሌና ነሐሴን  ስናስታውስ የመስፍን በቀለን ነይ በክረምቱና ሰኔን ስናስታውስ ደግሞ የአበበ ተካን እንደ ሰኔ ሰማይ እንደምንጠቅሰው ጥቅምትን ስናስታውስ ደግሞ የንዋይ ደበበን የጥቅምት አበባ እናወሳለን ሲል አጫውቶናል፡፡  

ሌላው ደግሞ ጥቅምት ወር የእሸት ወቅት ነው፡፡ በመስከረም የጀመረው አበባ ሙሉ በሙሉ የሚፈካበት፣ ቡቃያው ወደ እሸትነት የሚያድግበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ጥቅምት ወር  በእሸትም ታዋቂ ነው፡፡ በባህል ዘፈኖቹ በስፋት የሚታወቀው ድምጻዊ መብሬ መንግስቴ፡-

“የጥቅምት እሸት ነሽ የመስቀል አበባ

እባክሽ ነይልኝ ሳጣሽ ሆዴ ባባ…” እያለ ያቀነቀነውም ለዚህ ይመስላል፡፡

ጥቅምትን በቅኔ

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን “አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ” በተሰኘው ግጥሙ የጥቅምትን ወር ውበት፣ ናፍቆትና እሸት እጅግ ድንቅ በሆኑ ቃላትና ስንኞች ገልጾታል፡፡

“…ተግ ሲል ያንቺ ሽውታ

ብዥ ሲል እንደ አድባር ጥሪ፣ እንደተርብ ቅርስ ሽታ

እንደ እሳት ዳር ተረት ግርሻ፣ እንደ እንቆቅልሽ ትውስታ

የጥቅምት እሸት አወደ፣ ነቃ ደሞ ያንቺ ትዝታ…

አውድማው ተንተረከከ

ሰንበሌጥ ተንተረከከ

ነይ አክርማ እንነቃቅል

ከወንዛችን ሾላ ጠለል

ነይ ጢሎሽ እንጠላጠል

መስኮቻችን ሰብሎቻችን፥ ግጦሾቻችን አባቱ

የእቴቴሽ ላሞች አጋቱ

በሮቻችንም አጓሩ፣ ኮርማዎቻችንም ነቁ

ጊደሮቻችን ለጥቃት፣ ለይዘታ ለክብደት በቁ

የሁዳድ ድርቆሽ ሰፈር፣ ጥገቶቻችን ቦረቁ … እያለ ጥቅምትን ስእላዊ በሆነ፣ ወቅቱን በሚያስናፍቅና በትዝታ በሚያስረቀርቅ መንገድ ከትቦታል፡፡

ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ስለወራት በርካታ አባባሎች አሉ፡፡ ወቅቶችን፣ ሁኔታዎችንና ታሪካዊ አጋጣሚዎችን በኪነ ጥበብ የመግለጽ ባህል ከፍተኛ ነው፡፡ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ስለሆነው መስከረም፣ ለሞኝ ሰኔ በጋው መስረከም ክረምቱ፣ መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው… የሚሉት አባባሎች እንዳሉ ሁሉ ጥቅምትን የተመለከቱ  በርካታ ሥነ ቃሎች ተነግረዋል፡፡

ከዚህ አንጻር ጥቅምት በግጥም ብቻም ሳይሆን በአባባል እና በአጠቃላይ ፎክለርም የሚገለጽ ወር ነው፡፡ከአባባሎች ውስጥ በጣም ታዋቂው “በጥቅምት አንድ አጥንት” የሚለው ነው፡፡ በበርካታ ጋዜጦች፣መጽሔቶችና ሰነዶች ላይ እንደሰፈረው የጥቅምት ወር ከልምላሜ ፀጋው በተጨማሪ በማለዳው ውርጭ፣ በምሽቱ ቅዝቃዜና በሌሊቱ ቁርም ጭምር በደንብ ይታወቃል። እንዲሁም ቀን ቀን የሚወጣው ጠንከር ያለ ፀሐይ ሌላኛው የጥቅምት ወር መገለጫ ነው።

የጥቅምት ወር ብርድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ይሄንንም ብርድ ለመቋቋም ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችንና መጠጦችን የሰው ልጅ ማግኘት ይገባዋል። ከእነዚህ ምግቦች ውስጥ ደግሞ  ስጋ አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት የብርዱን ወቅት ተቋቁሞ ለማለፍና የስጋን አስፈላጊነት ለማንሳት “በጥቅምት አንድ አጥንት” የሚለው አባባል ተደጋግሞ ይሰማል፡፡

በጥቅሉ ወርሃ ጥቅምት አዕዋፋት ፍራፍሬ እና ጥራጥሬ እንደ ልባቸው እየተመገቡ በጋራ የሚዘምሩበት፣ የቤት እንስሳት በየቃርሚያው የተረሳ እሸት የሚመገቡበት ወር ነው፡፡ ፍሬ ነገር ስለሚበሉ የሚሰጡትም በዚሁ ልክ ነው፡፡ ወተት እና ቅቤ በጥቅምት እንደ ልብ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ሰፊ መልክዓ ምድር እና የተለያየ የአየር ንብረት ያላት እንደመሆኗ እሸት በተለያየ ጊዜም ሊኖር ይችላል። ለአብነትም በአገራችን ቆላማ አካባቢዎች እሸት የሚደርሰው ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ ጥቅምት ግን በብዙ መልኩ እና ውበቱ ይለያል። ጥቅምት ለእንስሳት የጥጋብ ወር ነው፡፡ የሀገሬ ሰው የጠገበ ሰው ሲያጋጥመው እገሌ “የጥቅምት ወይፈን ሆነ” ማለቱ ለዚሁ ነው፡፡ የወንዝ ውሃም ቢሆን ከምንጊዜውም በላይ ኩልል ብሎ የሚጠራው በጥቅምት ነው፡፡  ችግሩ የጥቅምት ውኃ ፈላጊው ትንሽ ነው፡፡ ምክንያቱም በብዙ ቦታ የወተት ወቅት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል “ውሃስ የጥቅምት ነበርሽ ማን በጠጣሽ” የሚባለው፡፡

በአጠቃላይ ጥቅምት ጥበባዊ መልኮች የያዘ ነው፡፡ በዚህም የጥቅምት ወር በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ የሀገራችን ማህበረሰቦች ዘንድ ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review