ጥበብን ከጥበበኛው አወዳጅ  ድባብ

ኢሬቻ ከጨለማ ወይም ከክረምቱ ወደ ብራማው ወቅት በሰላም መሸጋገርን አስመልክቶ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ከአሮጌ ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ፣ የብርሃን ዘመን የመምጣት ምልክት ነው፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ጊዜ የተለያዩ ሳቢ ቀለሞች የሚታዩበት፣ አበቦች የሚፈኩበት እንዲሁም ሜዳና ተራሮች አረንጓዴ የሚለብሱበት ነው፡፡ ህብረ ዝማሬውም የኪነ ጥበብ መንፈስን የሚያጋባ ነው። በዚህ ጽሑፍም ኢሬቻ ለኪነ ጥበብ ያለውን ፋይዳ እና በዓሉ በኪነ ጥበብ እንዴት እንደተገለጸ እንዳስሳለን፡፡

በኦሮሞ ባህል ማእከል የኪነ ጥበብ መምህር የሆነው ዳዲ ታምሩ በዓሉ ከተፈጥሮ ውበት በተጨማሪ የኦሮሞ ህዝብ እና ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች በባህል አልባሳት ደምቀው የሚሳተፉበት ነው፡፡

በኢሬቻ በዓል ላይ የተለያዩ ዘፈኖች ይቀርባሉ፡፡ ጣእመ ዜማዎች ይሰማሉ፡፡ እነዚህ የባህል  ዘፈኖች ለዘመናዊ ሙዚቃም መሰረት ናቸው፡፡ ዘፈኖቹም ኢሬቻን የሚያወድሱ፣ ፈጣሪን የሚያመሰግኑ እና ከክረምት ወደ ብራ መሸጋገርን የሚገልጹ ናቸው፡፡

የታዋቂው ሰዓሊ የግርማ ቡልቲ ኢሬቻ በዓል አከባበር የስእል ስራ

ስለ ኢሬቻ ከተዘፈኑ ዘፈኖች ውስጥ የድምጻዊ ጫላ ቡልቱሜ “WAGGAADHAAN NU GA’I” የተሰኘው ዘፈን ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። ይህ ዘፈን ኢሬቻ በደረሰ ቁጥር በሆቴሎችና በመገናኛ ብዙሃን በስፋት የሚደመጥ ነው፡፡ በዩትዩብ ብቻም ከ7 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች አይተውታል። የድምጻዊ አለሚቱ ስሜ፣ የአርቲስት ቀመር የሱፍ እና ገላና ጋሮምሳ ዘፈኖችም የኢሬቻ ውበት፣ ህብረ ብሄራዊ ቀለማት፣ ድምቀት እና ናፍቆት የተገለጸባቸው ናቸው፡፡

ኢሬቻ የሚከበርበት የመስከረም ወቅት ውብ ነው፡፡ ልዩ ነው፡፡ ማራኪ ተፈጥሮ፣ አረንጓዴ ጋራ፣ ጥርት ያለ መልካ የሚታይበት ነው፡፡ ኢሬቻን የሚያከብሩ ሰዎች አለባበሳቸው በቀለማት ያሸበረቀ እና ማራኪ ነው፡፡ የሚያዜሙት ዜማም ቀልብን የሚስብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለሌላ ኪነ ጥበባዊ ስራ የሚያነሳሳ ነው፡፡

ታዋቂው ሰዓሊ ግርማ ቡልቲ ከዚህ ቀደም ኢሬቻ  በስእል እንዴት ተገለጸ? በሚል ጉዳይ ላይ ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ባጋሩት ሃሳብ እንደገለጹት በኢሬቻ ሰሞን ብርሃናማ ቀለሞች በብዛት ይታያሉ፤ አደይ አበባ በመስኩ እና በጋራው ላይ ይፈካል፣ የሰው አለባበስም በቀለምና ጥበብ ያሸበረቀና የደመቀ ይሆናል፡፡ ወንዞች ንጹህ ይሆናሉ፡፡ በዙሪያችን የምናየው ሁሉም ነገር ውብ እና የተለያየ ቀለም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የኢሬቻ ሰሞን ተፈጥሯዊ አሳሳል ምርጫቸው ለሆኑ ሰዓሊያን ልዩ ወቅት ነው፡፡

የመስከረም ወር ልዩ ነው፡፡ ተፈጥሮ ዳግም የሚታደስበት፣ ብዙ አይነት ተፈጥሯዊ ቀለሞች የሚታዩበት ነው፡፡ በዚሁ ወር የሚከበረው ኢሬቻም ከተፈጥሮ እና ማህበረሰቡ ህይወት ጋር የተሳሰረ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ኢሬቻ የሚከበርበት ወቅትና በዓሉ በራሱ ተፈጥሮን፣ ህይወትን፣ ባህልና ታሪክን መሰረት አድርገው ለሚስሉ ሰዓሊያን የሃሳብ እና የቀለም አማራጮችን ለማግኘት የሚረዳ ነው። ይህም እኔን ጨምሮ ለሌሎች ሰዓሊያን የሃሳብ መነሻ ሆኖ አገልግሏል ብለዋል፡፡

እርሳቸው በስእል ስራቸው ኢሬቻን የሚገልጹት በተፈጥሯዊ የአሳሳል ዘይቤ “Realism Painting” ነው፡፡ በዓሉ ልዩ አይነት ቀለም፣ ባህል፣ ተፈጥሮ፣ አለባበስ እና ሌሎች ሁነቶች የሚታዩበት በመሆኑ ኢሬቻ ለሰዓሊያንና ለሌሎች የኪነ ጥበብ ሰዎች  ትልቅ የሃሳብ እና የእይታ ምንጭ ነው።

ሰዓሊው አክለውም በኢሬቻ ጊዜ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች ሁሉም ሰው በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለበዓሉ ብሎ የሚሰራ ልብስ አለ። በእነዚህ ልብሶች ላይ የሚታዩ ጥበቦችና ቀለሞች በጣም ማራኪ ናቸው። እነዚህ አልባሳት በስዕል ሲገለጹ ተፈጥሯዊ፣ ውብ፣ ሳቢ፣ ማራኪና ገላጭ ይሆናሉ፡፡ ከአልባሳት ባለፈ በዓሉ የሚከበርበት መልካ ወይም ወንዝ አለ፡፡ ኢሬቻ መልካ የሚከበረው በወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ የበጋው ኢሬቻ ወይም ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ በተራራ ላይ የሚከበር ነው። ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው የምስጋና ቀን መሆናቸው ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ሰዓሊዎች ወደ ወንዙ በመሄድ ማህበረሰቡ በዓሉን ሲያከብር ይታዘቡታል፡፡ ተራራዎችንም ሲመለከቱ ልዩ የሆነ ስሜት ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፤ በኪነ ጥበብ መገለጽ ያለበትና በእኔ የስእል ስራዎች የተንጸባረቁትም እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ይላሉ፡፡

“ይህን የመሰለ ገጸ በረከት እና ሁለንተናዊ አቅም ያለው  ኢሬቻ በኪነ ጥበብ የሚገባውን ያህል አልተገለጸም” የሚለው የኪነ ጥበብ መምህሩ ዳዲ ታምሩ፣  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች እንደሚስተዋሉ ያነሳል፡፡ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥም በየወቅቱ የሚዘጋጁ አውደ ርእዮችን መጥቀስ ይቻላል ይላል፡፡ የዘንድሮው የኢሬቻን በዓል የሚገልጹ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫሎችም የዚሁ ማሳያዎች መሆናቸውን አክሏል፡፡

ለአብነትም ከመስከረም 18 እስከ 24 በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ልዩ የኢሬቻ ኤክስፖ ተካሂዷል፡፡ በዚህ አውደ ርእይ ላይ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ ፎቶ ግራፍና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ስራዎች ቀርበዋል፡፡

በተመሳሳይ በዓሉን ምክንያት በማድረግ “ኢሬቻ እና ሥነ ጽሑፍ” በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሞ የሥነ ጽሑፍ ጉዞ ውስጥ ደማቅ አሻራቸውን ካኖሩና በተወዳጅ የግጥም ስራዎቻቸው አንቱታን ካተረፉ ደራሲያን እንዱ የሆነውን፣ የገጣሚ እና ፎክሎሪስት ዘላለም አበራ (ኦቦ አባ ጠዳ) “ኦቦምቦሌቲ” የተሰኘ አዲስ የአፋን ኦሮሞ፣ ግጥም መድብል ደርሷል።

በአብዛኛው በዓሉ ሲደርስ ኢሬቻን የተመለከቱ ቴአትሮች እና ፊልሞች ይሰራሉ። የስእል አውደ ርእዮች ይዘጋጃሉ፡፡ ሙዚቃዊ ተውኔቶች ይቀርባሉ፡፡ በእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ውስጥ ኢሬቻ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነትና እህትማማችነት፣ ለሰላም፣ ለምስጋና እና አብሮነት ያለው ፋይዳ ይንጸባረቅበታል፡፡

የኪነ ጥበብ  መምህሩ፣ “ኢሬቻ በብዙ ኪነ ጥበባዊ መንገዶች ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ይበልጥ የተገለጸው በሙዚቃ አማካኝነት ነው። ቆየት ያሉት፣ አዳዲስ ሙዚቃዎችም ስለ ኢሬቻ ተሰርተዋል። ፊልም እና ቴአትርም ከሙዚቃ ቀጥሎ በተወሰነ መልኩ እንዲሁ፣ በስእል ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ተንጸባርቋል፡፡” የሚለው ዳዲ ለአብነትም ከሰሞኑ የተመረቀውን “አቴቴ አያና ሐዎታ” የተሰኘውን ፊልም ጠቅሷል፡፡

“አቴቴ አያና ሐዎታ”  ዘጋቢ ፊልም  በገዳ ሥርዓት እና በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የሴቶች ሚና ያላቸውን ልዩ ወጎች፣ ፍልስፍናዎች እና ታሪካዊ ፋይዳዎች በጥልቀት ያሳያል። ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ የእናቶች አቴቴ ዘጋቢ ፊልም ታሪካችንን ከማስተዋወቅ ባለፈ በገዳ ስርዓት ውስጥ ሴቶች እና እናቶች ያላቸውን ልዩ ስፍራ አጉልቶ የሚያሳይ  እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡

“ይህ ፊልም ከኢሬቻ ጋር ግንኙነት ያለው ነው” የሚለው የኪነ ጥበብ መምህሩ ዳዲ ታምሩ፣ አሁንም የተለያዩ ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት ላይ የሚገኙ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ እንደነዚህ አይነት ፊልሞችን በቀጣይ በስፋት በመስራት ኢሬቻንም ሆነ ሌሎች የሀገራችንን በዓላትና እሴቶች ማስተዋወቅ ይገባል ሲልም ሃሳቡን ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል አጋርቷል፡፡

የኪነ ጥበብ መምህሩ ኢሬቻ ለኪነ ጥበብ ያለውን ፋይዳ ይበልጥ ለመጠቀም በርካታ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁሟል፡፡ ለአብነትም በኦሮሞ ባህል ማእከል በየሦስት ወሩ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቅሷል፡፡ ስልጠናው በውዝዋዜም፣ በቴአትር እና በሌሎች ዘርፎችም ነው፡፡ ክረምት ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ስልጠና ይሰጣል። በክረምት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተለያየ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ የሙዚቃ ማህበራትም በዚህ ስልጠና ላይ ይሳተፋሉ፡፡

ስልጠና የሚሰጡት መምህራን ከተለያየ ቦታ የሚመጡ ናቸው፡፡ ይህም ልምድና ሳይንስን ያጣመረ እንዲሆን ያደርገዋል። ስልጠናው ከቴአትር ባለፈም የስእል ስራን ያካተተ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ደግሞ እንደ ኢሬቻ  በዓላትን በኪነ ጥበቡ ውስጥ ለማንጸባረቅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ሲልም ማጠቃለያ ሃሳቡን አንስቷል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review