AMN – ህዳር 22/2017 ዓ.ም
እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጋር በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ በዛሬው ዕለት የሰላም ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
በመረሀ-ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ጋዛሊ አባ ሲመል፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮምሽነር ሌተናል ጄነራል ዲሪባ መኮንን፣ የኢትዮጵያ መከላከያ መረጃ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ታዋቂ አትሌቶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅትም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለመጡት ምስጋና አቅርበዋል።
ከጦረኞች በላይ ጦርነትን የሚያባብሱት ስለጦርነት የማያውቁ ናቸው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ እኔ ካለኝ ልምድ አንፃር ጦርነት ጎጂ በመሆኑ የሰላምን መንገድ መርጣችሁ በመምጣታችሁ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ተግባር በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕስ መስተደድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ የኦሮሞ ህዝብ በባህልና በወጉ መሰረት በሬዎቹን ጠምዶና ፈረሶችን ጭኖ በመውጣት ሰላም ይውረድ ባለው መሰረት ጥሪውን ተቀብላችሁ በመምጣታችሁ በራሴና በክልሉ መንግስት ስም አመሠግናለሁ ብለዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ የመከላከያ ሠራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህ ዓለም የሰው ልጅ የፖለቲካ ልዩነት ያለው መሆኑን ያወሱት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ እኛም ያለንን የፖለቲካ ልዩነት በጠመንጃ ከመፍታት በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ወስነን ነው ስምምነቱን የመረጥነው ብለዋል።
ይህ ስምምነት ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም ማገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።