ባለፉት ዓመታት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን 2ኛውን የአካባቢ ብክለትን መከላከል መርሐ-ግብር አስጀምሯል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት አመራሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች፣የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ባለፉት ዓመታት ፅዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አቶ አደም አክለውም ጽዱ ኢትዮጵያ ምርታማነትን በማሳደግ ማህበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር፣ የከተማ ኮሪደር ልማት፣ የገጠር ኮሪደር ልማት፣ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምን ማስፋፋት፣ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ዘዴዎች ማስፋፋት እና የህግ እና ተቋም ግንባታ ስራዎች በስፋት ሲከናወኑ እንደነበር እና በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ በዘርፉ ባከናወነችው ስራ እውቅና የተሰጣት ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤም እውቅናውን ተቀብለዋል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፣ አዲስ አበባ ከተማ ጽዱ አከባቢን ከመፍጠር ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን እና አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ልማት ከለውጡ በፊት የነበረውን የ2.8 በመቶ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ወደ 20 በመቶ ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በከተማ ደረጃ 76 ወንዞች እና ጅረቶች እየለሙ እንደሚገኙ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ 44 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
እነዚህ ወንዞች ከመበከላቸው የተነሳ የህዝቡን ጤና ሲያወኩ የነበሩ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ በተከናወኑ ስራዎቻ ወንዞቹ ወደ ቀደመ ይዘታቸው እየተመለሱ እደሚገኙ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመንገድ ላይ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት፣ ዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃዎችን መገንባት እና ሌሎች የአካባቢ ብክለት መከላከያዎችን በመዘርጋት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ንቅናቄው ለ6ወራት የሚቆይ 6 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር የንቅናቄ መርሐ-ግብር በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።
ፅዱ ኢትዮጵያን የመፍጠር ጉዳይ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አይደለም ያሉት ኃላፊዋ፣ የመላውን ማህበረሰብ ተሳትፎ እና ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል።
በሀብታሙ ሙለታ